Articles and Views

Home         Mission      Coffee House        Radio & TV        Entertainment        Contact         Photo Gallery

ሊበራል ዴሞክራሲ ወይስ አብዮታዊ ዴሞከራሲ?

መርስኤ ኪዳን

ሰሞኑን በተለያዩ ኢትዮዽያ ተኮር ድረ-ገፆች ላይ በሊበራል ዴሞክራቶችና እና በ አብዮታዊ ዴሞክራቶች መካከል የጦፈ ክርክር በመካሄድ ላይ ይገኛል። ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግና ደጋፊዎቹ ሊብራል ዴሞከራሲ እንከተላለን በሚሉ ተቃዋሚዎች ላይ የሰላ ትችት በመሰንዘር ላይ ይገኛሉ። ጠቅላይ ሚኒስትራችንን ጨምሮ የ ኢህአዴግ መሪዎቸና ተከራካሪዎች ሊበራል ዴሞከራሲን በራሱ ሳይሆን ኒዮሊበራሊዝምን እንደ ሊበራል ዴሞክራሲ መገለጫ አድርገው በማቅረብ ተችት ለመሰንዘር ሲሞክሩ ይታያሉ። አንዳንዶቹ ሊበራል ዴሞክራሲን አዛብቶ በመተርጎም ሳይገቱ ጭራሽ የ አብዮታዊ ዴሞከራሲ ፈልሳፊ ነን። አብዮታዊ ዴሞከራሲ በኢህአዴግ የተፈለሰፈ አገር በቀል አስተሳሰብ ነው ሲሉ ተደምጠዋል፣ ተነብበዋል። በሊበራል ዴሞክራቶች በኩል እንደተለመደው አብዮታዊ ዴሞክራሲን የመተቸቱ ነገር ቢታይም ሊበራል ዴሞክራሲን የተሻለ አማራጭነት በማሳየት በኩል ከ አይን የሚገባ ክርክር ሲደረግ አላይሁም። በዚች አጭር ፅሁፍ በማውቀውና በምረዳው መጠን በ አብዮታዊ ዴሞከራሲ እና በሊበራል ዴሞከራሲ አማራጭነት ዙሪያ እንዲሁም ኢህአዴጎች ከሊበራል ዴሞክራሲ ጋር ሊያያይዙት በሚሞከሩት በኒዮሊበራሊዝም ዙሪያ ያለኝን ሃሳብ እንደሚከተለው አቀርባለሁ። 

 

አብዮታዊ ዴሞከራሲ

በተከታታይ ሳምንታት በተካሄዱት የ2002 ምርጫ ክርክሮች የኢህአዴግ ተከራካሪዎች ከዚህ ቀደሙ በተለየ መልኩ አብዮታዊ ዴሞክራሲን እንደራሳቸው ፍልስፍና አድርገው ለማሳየትና ከእውነተኛ ምንጩ ከሶሺያሊዝም በተቻለ መጠን ለማራቅ ሲጥሩ ተመልክተናል:: መቸም አብዛኛው ሰው ፖለቲካን በወጉ አይከታተልም ወይም አያነብም ከሚል አስተሳሰብ ነው እንዲህ ያለ ከእውነታው እጅግ የራቀ ክርክር ለመከራከር የተጋበዙት::  የአለም ፖለቲካዊ ሂደትን በአለፍ ገደም የሚከታተል ሰው እንኳ የአብዮታዊ ዴሞክራሲን ምንጭ ማወቁ አይቀርም:: አብዮታዊ ዴሞክራሲ በ1917 ዓ.ም. በተካሄደው የሶቪየት ህብረት የሶሺያሊስት መንግስት ምስረታ የንድፈ ሀሳብ (Theory) መመሪያ ሆኖ እንዳገለገለ ይታወቃል:: 2

በቭላድሜር ሌኒን የተነደፈው ይኸው ንድፈሀሳብ በማርክስና በኤንግልስ ንድፈሀሳቦች ዳብሮ በአለም አቀፍ ደረጃ በብዙ አገሮች ተቀባይነትን አግኝቶ ማርክሳዊ ሌኒናዊ ፍልስፍና በሚል ለመታወቅ በቅቷል:: ሌኒን በካፒታሊስት ኢኮኖሚያዊ ደረጃ ላይ ለሚገኙት “ሶሺያሊስት ዴሞክራሲ” የሚባለውን ንድፈሀሳብ ሲያቀርብ በካፒታሊስትነት ደረጃ ላልደረሱ አገሮች “አብዮታዊ ዴሞክራሲ” የሚባለውን አቅርቧል::  ለዚህም መሰረታዊው ምክንያት ለሶሺያሊስት አብዮት መነሻ የሆነው የሰራተኛው መደብና የቡርዣው ተቃርኖ በካፒታል ባላደጉት አገሮች ሊታይ ባለመቻሉ ከሰራተኛው መደብ ሌላ ቡርዥዋውን የሚታገሉ አካላትን (አርሶ አደሩን ና ንዑስ ከበርቴውን) የሚያስተባብር አብዮት ለመፍጠር መሆኑ ነው::  ለዚህም ማረጋገጫው ኢህአዴግ በ1984 ባሳተመው "አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ" ፕሮግራሙ የሚከተለውን አስፍሯል:: "ላብ አደሮች; አርሶአደሮችና የከተማው ንዑስ ከበርቴ በአብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ለውጦች የተሟላ ጠቀሜታ ያገኛሉ::" ይላል:: በዚያው ፕሮግራሙ ላይ ቡርዥዋውን በተመለከተ "የሰፊው ህዝብ ስልጣን ሰፊው ህዝብ ወሳኝ የሚሆንበት ሁኔታ የመፈጠር ጉዳይ እጅግ ስለሚያሳስበውና ስለሚያሰጋው በጸረ አብዮት ካምፕ የሚቀላቀልበት ሁኔታ ይኖራል:: ቡርዥዋ ከጸረ ዴሞክራሲ ሀይሎች ጋር በሚሰለፍበት ጊዜ መብቱ ሊገደብ የግድ ይሆናል..." ይላል::  ይህ እንግዲህ የማርክሳዊ ሌኒናዊ አስተሳሰብ ዋና መገለጫ ነው::

ኢህአዴግን የመሰረቱትን ድርጅቶች ማንነት ስናይ ደግሞ የኢህአዴግ ማርክሳዊ ሌኒናዊ አስተሳሰብ ታሪካዊ መነሾ ይገለጽልናል:: ኢህአዴግን የመሰረቱት ሁለት ፓርቲዎች ማለትም ሕወሓት እና ኢህዴን በጊዜው ማርክሳዊ ሌኒናዊ መሆናቸው የሚታወቅ ነው:: በተለይ ሕወሓት ኢህአዴግን ከመመስረቱ በፊት በ1977ዓ.ም ማርክሲስት ሌኒኒስት ሊግ ትግራይ (ማሌሊት) የሚባለውን ፖለቲካዊ አመራር ከንፍ በማቋቋም ዝግጅት አድርጓል:: ማሌሊት በፕሮግራሙ ሁለተኛ ክፍል አገር አቀፍ ማርክሳዊ ሌኒናዊ ግንባር መመስረትን እንደ አላማው አስቀምጧል:: ሁለቱ ፓርቲዎች ግንባር ሲፈጥሩ የሌኒንን ንድፈሀሳብ በመውሰድ በኢትዮዽያ ካፒታሊስት ስርአት ባለመኖሩ ምክኒያት በ ማርክሲስት ሌኒኒስት አስተሳሰብ ለእንዲህ አይነት አገሮች ተስማሚ ተብሎ የተመረጠውን አብዮታዊ ዴሞክራሲን እንደመመሪያቸው መርጠዋል:: ስለሆነም የግንባራቸውን ስያሜ “የኢትዮዽያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር” ብለውታል::

ሆኖም ከአለማቀፍ ፖለቲካዊ ሚዛን ለውጥ በመነሳት ኢህአዴግ አንዳንድ መሰረታዊ ለውጦች ለማድረግ ተገዷል:: ዋነኞቹ ሁለት ለውጦች ናቸው:: አንደኛው መድበለ ፓርቲ ስርአትን መቀበሉ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ነጻ ገበያንና ካፒታሊዝምን እንደ ኢኮኖሚያዊ ስርአት ተቀብሏል:: ስለሆነም ኢህአዴግ የሚከተለው አብዮታዊ ዴሞክራሲ በማርክሳዊ ሌኒናዊ ማእቀፍ የሚታይ ሆኖ አንዳንድ የካፒታሊዝምንና ሊበራል ደሞክራሲን አስተሳሰቦች የተቀበለ ነው::  

 

ኒዮ-ሊብራሊዘም አዲሱ ጭራቅ

በመጀመሪያ መታወቅ ያለበት አብዮት የሚያስፈልግበት ሁኔታ ባለበት ጊዜ አብዮት ማድረግን የምስማማበት ሲሆን ሕወሓትም ደርግን ለማሸነፍ ያደረገውን ተጋድሎ የማደንቅ ነኝ:: ሆኖም ኢህአዴግ ለአመጽ ተስማሚ የሆነውን አብዮታዊ አስተሳሰብ አገር ለመምራት መጠቀሙን እቃወማለሁ ለዚህም ምክኒያቱ አንድን አካል በጠላትነት ማየትን የሚያስገድደው አብዮታዊ ዴሞክራሲ ለሁሉም የአገሪቱ ዜጎች በእኩል የሚሰራ መንግስት ለመፍጠር አያስችልም ብየ ስለማስብ ነው:: 

ኢህአዴግ መድበለ ፓርቲ ስርአትን መቀበሉ እሰየው የሚያሰኝ ቢሆንም የሚከተለው “አብዮታዊ ዴሞክራሲ”   ዴሞክራሲን በማስፈን ረገድ አንዳንድ መሰረታዊ ችግሮች አለበት:: አብዮታዊ ዴሞክራሲ ማርክሳዊ ሌኒናዊ አስተሳሰብ እንደመሆኑ መጠን በሁለት ወይም ከዛ በላይ በሆኑ የህብረተሰቡ ክፍሎች የሚፈጠርን ተቃርኖ የሚመረኮዝ አስተሳሰብ ነው:: ስለሆነም በየትኛውም ጊዜ እወክለዋለሁ ለሚለው የህብረተሰብ ክፍል ጠላት ይፈልግለታል::  ለምሳሌ በ60ዎቹ ባላባቱ ከበርቴውና ኢምፔሪያሊስት ሀይሎችን እንደጠላት ያይ ነበር:: የ66ቱን አብዮት ከህዝብ የነጠቀው ደርግ በሚያሳዝን ሁኔታ አገሪቱን ሊያሳድግ ይችል የነበረውን ከበርቴ ከባላባትና ጨቋኝ ባልለየ ሁኔታ ሁሉንም በጠላትነት በመፈረጅና በማሳደድ የአገሪቱን ኢኮኖሚ አንኮታኩቷል:: ከዚያም ደርግ ራሱ በጠላትነት ተፈርጆ አብዮት ተካሄደበት:: ኢህአዴግ ከስልሳዎቹ ጀምሮ የሚመራበት ማርክሳዊ ሌኒናዊ ፍልስፍና እያስገደደው በተለያየ ጊዜ ጠላት እየፈጠረ ሲያጠቃ ቆይቷል:: በመጀመሪያ ኢህአፓ; ኢዲዩና የኤርትራው ጀብሀን በጠላትነት አጠፋ:: ከዚያም ደርግን በጠላትነት ተዋጋ; ከዚያም የመሀል አገሩን ምሁርና ልሂቅ ትምክህተኛ በሚል በጠላትነት መደበ:: እነኚህን ሁሉ በጠላትነት በመመደብ አላቆመም ለህዝብ የጭራቅ አምሳያ እንደሆኑ አድርጎ በመቀስቀስ እነሱን ማጥፋት እንደመፍትሄ እያስቀመጠ ነው የመጣው:: ይህ ባህሪ የሕወሓት ወይም የኢህአዴግ ብቻ ሳይሆን የአብዛኞቹ የስልሳዎቹ ፖለቲከኞች ባህሪ ነው:: (የኢህአዴግ ጠላት የሆኑትም በተመሳሳይ መልኩ ወያኔን ጠላት አድርገው ጭራቅ አድርገው ሊስሉልን ይፈልጋሉ:: )

ኢህአዴግ ወይም ማንኛውም አብዮታዊ አስተሳሰብ ያለው ፓርቲ ጠላትን የግድ ለምን እንደሚፈልግ ይገርም ይሆናል:: ምክኒያቱን ጠለቅ ብለን ስናየው ግን ይገባናል:: አብዮታዊው ፓርቲ ህብረተሰቡን አንድ የጥቅም ተቃርኖ (conflict of interest) ያለው ጠላት ይፈጥርለትና ያ ጠላት ተብየው ክፍል ከሌላው ህብረተሰብ ጋር ካለው የጋራ እሴት ይልቅ ተቃርኖውን አጉልቶ በማሳየት እንደጭራቅ አድርጎ ይስለውና ህብረተሰቡን ከዚያ ጠላት ሊታደገው የሚችለው ፓርቲ እሱ ብቻ መሆኑን በመደስኮር ስልጣኑን ለረጅም ጊዜ ማስቀጠል እችላለሁ ብሎ ከማሰብ የሚመጣ ነው:: ታዲያ ባገር ውስጥ ያሉ ሀይሎችን በበላይነት እንደቀጣ ያወቀው ኢህአዴግ አሁን ደግሞ አዲስ ጠላት በመፈለግ ላይ ይገኛል:: ሰሞኑን እንደሚታየውና እንደሚሰማው አዲሱ ጭራቃችን ኒዮሊበራሊዝም ነው:: ኢህአዴግ ኒዮሊበራሊዝም እያለ የሚገልጸው አስተሳሰብ በመሰረቱ ራሱን የቻለ አስተሳሰብ ሳይሆን; በምእራቡ አለም የሚገኙ ሀያላን አገሮች እነሱ በካፒታሊስት ስርአትና በነጻ ገበያ ከበቂ በላይ ካፒታል አከማችተው ሲያበቁ ያላደጉ አገሮችን ከነሱ ነጋዴዎች ጋር እንዲወዳደሩ የሚያስገድድ እንዲሁም በተለያየ መልኩ ተጽእኖ የሚያደርጉ ፖሊሲዎችን እንዲያወጡ ለማስገደድ በነሱ ቁጥጥር ስር ባሉ እንደ አለም ባንክና አይ ኤም ኤፍ የመሳሰሉ ድርጅቶችን በመጠቀም የሚያስፈጽሙበት መመሪያ ነው::

በርግጥ እነኚህ ሀብታም አገራት ያለውን ሁኔታ (status quo) ባለበት እንዲቀጥል ይፈልጉ ይሆናል:: ማለትም እነሱ ሀብታም እኛ ድሀ እንደሆንን:: በተለይም ነጋዴዎቻቸው የድሀዎቹን አገሮች ሀብት የሚቆጣጠሩበትን መንገድ ከመፈለግ እንደማይቦዝኑ መገመት አይከብድም:: ግን እነሱ ብቻ ሳይሆኑ ማንኛውም ሀይል ጥቅሙን ለማስጠበቅ መጣሩ የማይቀር ነው:: ስለሆነም አላማቸውንና ስራቸውን በጥንቃቄ ማየት ቢጠቅምም በዚያው መጠን ከነሱ ጥሩ ነገር አይመጣም ብሎ ማሰብም ስህተት ነው:: በተቻለ መጠን ጥቅማችንን ባላሳጣ መልኩ ለጋራ ጥቅም አብሮ መስራት የሚቻልበትን መንገድ መፈለግ ያሻል::  እነኚህን ሀይሎች እንደ አንድ ጥቅሙን ማስጠበቅ እንደሚፈልግ የአለም ህብረተሰብ አካል ማየትና የራስን ጥቅም ባስጠበቀ መልኩ በጋራ መስራት ይገባል እንጂ እንደ ጠላት ማየት አይገባም:   

ሊበራል ዴሞክራሲ ከኒዮሊበራል ሀይሎች ጋር ያለው ግንኙነት ምንድነው የሚለውን ያየን እንደሆነ መልሱ ቀላል ነው:: እነሱ እንዲህ ተጽእኖ ማሳደር ከሚችሉበት ደረጃ እንዲደርሱ የረዳቸው ስርአት ሊበራል ዴሞክራሲ ነው:: ከሊበራል ዴሞክራሲ ስርአት ውጭ የነበሩ አገሮች ቁልቁል በሄዱበት ጊዜ ሊበራል ዴሞክራሲን ያሰፈኑ የምእራብ አውሮፓና የሰሜን አሜሪካ አገራት ግን ይኸው በአለም ኢኮኖሚም ሆነ ፖለቲካ የበላይነታቸውን ተቀዳጅተዋል::

 

ሊበራሊዝም

ምናልባት የኢህአዴግን ሆን ተብሎ የተዛባ ትርጉም ያደመጠ ሰው ታዲያ ኒዮሊበራሊዝም የሊበራል ዴሞክራሲ መገለጫ ካልሆነ ሊበራል ዴሞክራሲ ምንድነው? የሚል ጥያቄ ሊያነሳ ይችላል:: ሊበራሊዝም ከ18ኛው ክ/ዘመን ጀምሮ እንደያገሩና እንደጊዜያቱ እየታደሰና እየሰፋ የመጣ ሀሳብ ነው:: በአሁኑ ጊዜ ሊበራል የሚለው ስያሜ በተለያዩ አገራት የራሱ ትርጉም አለው:: ለምሳሌ በአሜሪካን አገር ያሉት ሊበራሎች በዋነኝነት አዳዲስ ማህበራዊ እሴቶችን ለመቀበል ባላቸው ዝግጁነት የተሰጣቸው ስያሜ ነው:: ስለዚህ ሊበራልነት ላዳዲስ አስተሳሰቦች ክፍት በመሆን ሊገለጽ ይችላል:: በሌላ በኩል በ19ኛውና 20ኛው ክ/ዘመን የገበያ ሊበራሎች በዝተው ነበር:: ይህም በገበያው የመንግስት ተሳትፎ እንዳይኖር የሚጥሩትን ያካትታል:: ከጅምሩ ጀምሮ እስካሁን ያልተለወጠውና የማንኛውም ሊበራል ዴሞክራሲ አስተሳሰብ መገለጫ የሆነው የግለሰብ መሰረታዊ ሰብአዊ መብትና ሀብት የማፍራት መብት መከበር ነው::

ምንም እንኳ ሊበራሊዝም መነሻው የግለሰብ መብትን ለማስከበርና በተለይም የመንግስትን ጣልቃገብነት ለመቀነስ ቢሆንም አሁን በሀያአንደኛው ክፍለዘመን ሊበራሊዝም በአንዳንድ በአውሮፓ ካሉ የሶሺያል ዴሞክራሲ አስተሳሰቦች ጋር በመዋሀድ ሊበራል ዴሞክራሲ የሚባል አስተሳሰብ ሆኗል:: ስለሆነም ሊበራል ዴሞክራሲ በመሰረቱ የግለሰብ መብትን በማስከበር ላይ ያተኮረ ሆኖ መንግስት እንደያስፈላጊነቱ የህብረተሰቡን ጥቅም ለማስጠበቅ ጣልቃ የሚገባበትን ሁኔታም ይቀበላል:: ስለሆነም የሀያአንደኛው ክ/ዘመን ሊበራል ዴሞክራሲ ዋነኛ መገለጫዎች

 የግለሰብ መብት መከበር ለአዳዲስ ማህበራዊ እሴቶችና አስተሳሰቦች ክፍት መሆን እና የአናሳም ሆነ የብዙሀን አስተሳሰቦች መከበር (መቻቻል)ናቸው:: ይህን ይዘን በኢትዮዽያ የሊበራል ዴሞክራሲ አራማጅ ማነው የሚለውን እንይና እንመለስበታለን::

 

ሊበራል ዴሞከራት ማነው?

በአሁኑ ጊዜ በአገራችን በኢትዮዽያ ከስልሳ የማያንሱ ፓርቲዎች አሉ:: ከነኚህ ፓርቲዎች አብዛኞቹ በብሄር እንጂ በአይዲዮሎጂ የተሰባሰቡ አይደሉም:: ህብረብሄራዊ ሆነው ከተደራጁት ውስጥም አብዛኞቹ በደፈናው ኢህአዴግን ለመቃውም እንጂ የተወሰነ አይነት አይዲዮሎጂን በመከተል አልተደራጁም:: በ2002ቱ ምርጫ ከተሳተፉት ፓርቲዎች መካከል ዋነኞቹን እንይ:: መአኢአድን ስንመለከት በዋነኝነት የመኢአድ አመሰራረት የኢህአዴግን በብሄር ላይ የተመሰረተ የመንግስት አወቃቀር በመቃወም የተመሰረተ ነው:: ይህ ፓርቲ መኢአድ ከመሆኑ በፊት በአማራው ላይ የሚደርሰውን ጥቃት ለመታደግ የተቋቋመ ነበር ስሙም መአህድ ነበር:: ከመአህድ አባላት በብሄር መደራጀት አይበጅም ብለው ያሰቡ ናቸው መኢአድን የአቋቋሙት:: በመሆኑም የመኢአድ ዋነኛ አጀንዳ የብሄር (የጎሳ) ፖለቲካን መቃወም ነው:: መኢአድ እስከቅርብ ጊዜ ድረስ ሊበራል ዴሞክራሲ የሚለውን አስተሳሰብ እንኳን ሊያራምድ ቃሉም በፕሮግራሙ አይገኝም ነበር::

ለ1997ቱ ምርጫ ቅንጅትን ከመሰረቱት ፓርቲዎች መሀል ለመጀመሪያ ጊዜ በፕሮግራሙ ላይ ሊበራል ዴሞክራሲን እንደመመሪያው አድርጎ የቀረበው በጊዜው በዶ/ር አድማሱ ገበየሁ የሚመራው ኢዴኣፓ መድህን (ኢዴፓ) ነው:: መኢኣድ በጊዜው ይሄ ነው የሚባል አይዲዮሎጂ አልነበረውም:: የቀድሞውን ቅንጅት ከመሰረቱት አራቱ ፓርቲዎች ዋነኞቹ ኢዴፓና መኢአድ መሆናቸው እንደተጠበቀ ሆኖ ከተቀሩት ውስጥ ቀስተደመና የሚባለው የነ ዶ/ር ብርሀኑ ፓርቲ ሶሺያል ዴሞክራሲን ይከተል ነበር:: ከፋም ለማም ቅንጅት ውስጥ ከነበሩት ፓርቲዎች ባይዲዮሎጂ የጠራ አቋም ይዞ የነበረውና በዚያም መሰረት ማኒፌስቶ አዘጋጅቶ የነበረው ኢዴፓ ነበረ:: ቅንጅት የኢዴፓን ማኒፌስቶ ያላንዳች ለውጥ እንዳለ በመውሰድ የቅንጅቱ ማኒፌስቶ እንዲሆን አድርጓል:: ለማንኛውም ከአራቱ የቅንጅት ፓርቲዎች ሊበራል ዴሞክራሲንም ሆነ ሌሎች አማራጮችን በመተንተን ከስድስት መቶ ግጽ በማያንስ የፕሮግራም ትንታኔው በዝርዝር በማየት ሊበራል ዴሞክራሲን እንደመመሪያው ይዞ የቀረበው ኢዴፓ ብቻ ነው:: በ2002ቱ ምርጫ ተሳታፊ የሆኑት እንደ አንድነት ቅንጅትና መኢአድ ያሉት የቅንጅትቅሪቶች በሙሉ ሊበራል ዴሞክራሲን በውሉ ተንትነው ተረድተው ሳይሆን ኢዴፓ ያቀረበውን የቅንጅት ማኒፌስቶና አይዲዮሎጂ እንዳለ በመውሰድ ነው::

አሁን መድረክ የሚባለው የፓርቲዎች ስብስብ ውስጥ ያሉት ፓርቲዎችና ግለሰቦች በሙሉ በስልሳዎቹ ገኖ በነበረው በ ማርክሲዝም ሌኒንዝም ጥርሳቸውን የነቀሉ ከመሆናቸው አንጻር ሊበራል ዴሞክራሲን የማራመድ ከልብ የሆነ ፍላጎት ቢኖራቸው እንኳ አብሮዋቸው ያደገው አመለካከት ሊለቃቸው ይችላል ብሎ ማሰብ ይከብዳል:: ከልባቸው ነው፤ አመለካከታቸውን እየቀየሩ ነው፤ የሚለው አስተሳሰብ በተግባር ሲታይ ምኞት ብቻ ነው:: ለምሳሌ አቶ ስየ አብረሀና ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ አንድነት የሚባለውን ፓርቲ ሲቀላቀሉ አንድነት በፕሮግራሙ ያሰፈረውንና የሊበራል ዴሞክራሲ ዋነኛ መገለጫ የሆነውን የግለሰቦች መብት መከበርን በማስቀየር የማርክሲዝም ዋነኛ መገለጫ በሆነው በቡድን መብት ተክተውታል:: በተግባር የሚታየው ማርክሲስቶቹ ወደሊበራል መቀየራቸው ሳይሆን ሊበራል ነን ይሉ የነበሩት ማርክሲስታዊ አስተሳሰብን እንዲቀበሉ መገደዳቸውን ነው::

ሌላው በመድረክ ውስጥ የሚገኙት የቀድሞ ማርክሲስቶች ሊበራል ደሞክራሲን እንዳልተቀበሉ ወይም እንዳልገባቸው የሚያሳየው የሚያራምዱት አቋም ነው:: ሁል ጊዜ አብዮተኞች (ማርክሲስት ሌኒኒስቶች) ራሳቸውን የህዝብ ጠበቃ አድርገው ከነሱ ውጪ ያሉትን የህዝብ ጠላት አድርገው ማሳየት ይፈልጋሉ:: አሁንም የመድረኮቹ ሊበራል ነን ባዮች በተግባር ራሳቸውን ብቻ የለውጥ ሀዋሪያ በማድረግ ሌሎቹ ፓርቲዎች በሙሉ ጠላት ከሆነው ከኢህአዴግ ጋር የተባበሩ ናቸው ብለው የተለመደውን የአብዮተኞች የሁለት ቡድን ተቃርኖ ለመፍጠር በመጣር ላይ ይገኛሉ:: ሊበራል ዴሞክራሲ ሌላው ዋነኛ መገለጫው የተለያዩ አመለካከቶችን የማስተናገድ ባህሪው ነው:: ለመድረኮች ግን ወይ የነሱ ወይ የኢህአዴግ አማራጭ ብቻ ነው ያለው:: መሀል ሰፋሪ ብሎ ነገር የለም:: ስለሆነም መድረክም ቢሆን ሊበራል ዴሞክራት ሊባል የሚችል ፓርቲ አይደለም:: ምናልባት ከኢህአዴግ ጋር የተሻልን ማርክሲስት ነን ብለው ቢፎካከሩ የበለጠ ያምርባቸዋል::

ባገራችን ካሉ ፓርቲዎች ሊበራል ዴሞክራሲን በውሉ ተረድቶ ከሌሎች አማራጮች አወዳድሮ መመሪያ ርእዮተአለሙ ያደረገው ኢዴፓ ብቻ ነው ማለት ይቻላል:: ኢዴፓ ከስድስት መቶ ገፅ በሚበልጥ የፕሮግራም ትንታኔው በአለም ያሉ ታሪካዊ ፖለቲካዊ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታዎችን ከግምት አስገብቶ ባደረገው ጥናት ለአገሪቱ የሚበጀው ሊበራል  ዴሞክራሲ እንደሆነ መደምደሚያ ላይ ደርሷል።  ሆኖም አሁን አገሪቱ ካለችበት ነባራዊ ሁኔታ አንፃር ሊብራል ዴሞከራሲና ነፃ ገበያ የሚደረስባቸው ግቦቸ እንጂ አሁን ወዲያውኑ ሊተገበሩ እንደማይችሉ ትንታኔው ላይ አስፍሯል። ስለሆነም በ አገራችን ያሉትን አራቱን ዋናዋና ፓርቲዎች በዋነኛ መገለጫቸው እንግለፃችው ከተባለ ኢህአዴግ አብዮተኛ፣ መድረክ ፌደራሊስት፣ መኢአድ የ አንድነት (ዩኒታሪስት)፣ ኢዴፓ ደግሞ ሊበራል ዴሞከራት ናችው ማለት ይቻላል። በ አይዲዮሎጂ መሰረታዊ ልዩነት የሚታየው በ ኢዴፓና በ ኢህአዴግ መካከል ነው ማለት ነው።

 

ለኢትዮዽያ የሚበጀው የቱ ነው?

መሰረታዊ የ አይዲዮሎጂ ልዩነት ያለው በ ኢህአዴግ (አብዮታዊ ዴሞክራሲ) እና በ ኢዴፓ (ሊበራል ዴሞክራሲ) መካካል መሆኑን ካየን ዘንዳ ለ ኢትዮዽያ የሚበጀው የቱ ነው የሚለውን ለማየት እንሞክር። ሁለቱም ጠንካራና ደካማ ጎን አላቸው። ባንድ በኩል አብዮታዊ ዴሞክራሲ እንደ ኢትዮዽያ በኢኮኖሚ እጅግ ኋላ የቀሩ አገሮች በፍጥነት ኢኮኖሚያቸውን ለማሳደግ ይችሉ ዘንድ መንግስት የአገሪቱን ሀብትና ጉልበት በመቆጣጠርና በተገቢው ቦታ በማዋል ፈጣን እድገት ማምጣት የሚችሉበትን ሁኔታ ለመፍጠር ያስችላል:: ይህ አመለካከት በተለይ ቻይና እጅግ ፈጣን የሆነ እድገት ያመጣችበት ሁኔታ የበለጠ እንዲጠናከር አስችሎታል:: ነገሩን ጠለቅ ብሎ ላየው ቻይና ብቻ ሳይሆን እንደ ጃፓን ያሉ አገሮችም ዴሞክራሲን ባሰፈኑበት ጊዜ ሳይሆን በአንድ ፓርቲ የበላይነትለረጅም ጊዜ በተመሩበት ጊዜ ነው ፈጣን እድገት ያስመዘገቡት:: በተለይ ባገራችን አለ ሊባል የማይችለውን መሠረተ ልማት በማስፋፋት ረገድ ዘላቂነት ባለው መልኩ የ አገሪቱን ሃብትና ጉልበት አስተባብሮ ለረጅም ጊዜ መገንባት ይጠይቃል። ስለሆነም ኢህአዴግ አቶ መለስ "African development: dead ends and new beginnings" ብለው በሰየሙት ረቂቅ ጽሁፋቸው እንደተነተኑት የነቻይናንና የደቡብ ኤሽያ አገሮችን አርአያ መከተል ይፈልጋል:: አብዮታዊ ዴሞክራሲ ፈጣን የ ኢኮኖሚ እድገት ለማምጣት እድል የሚፈጥርበት ሁኔታ ጥንካሬው ቢሆንም በዚያው መጠን ዴሞክራሲን ከማስፈን አኳያ ድክመቶች አሉት። አሁን ባገሪቱ እንደሚታየው ኢህአዴግ ለረጅም ጊዜ ስልጣኑን ይዞ ለመቀጠል ፍላጎት ስላለው ለዚያ አላማው ስጋት የሆኑትን ነገሮች በሙሉ ያፍናል። ለዚህ ዋና ምሳሌ የሚሆነው የሜዲያ ጉዳይ ነው። የግል ሬዲዮና ቴሌቪዥን ጣቢያዎች ቢከፈቱ ስጋት ይሆኑብኛል ብሎ ስለሚያስብ ይኸው አፍኖ ይዞታል። በርግጥ ኢህአዴግ ባገራችን ለመጀመሪያ ጊዜ የዴሞክራሲ ጭላንጭል ያሳየ ፓርቲ በመሆኑ ሊመሰገን ቢገባውም አገሪቱ በዴሞከራሲና ሰብአዊ መብት ማከበር መጓዝ የሚገባትን ያክል እንዳትጓዝ የ ኢህአዴግ አብዮታዊ ዴሞክራሲ እንቅፋት ሆኖባታል።

በሌላ በኩል ሊብራል ዴሞክራሲ የ አስትሳሰብ ነፃነትን የሚያበረታታ ርእዮተአለም ነው። ሊበራል ዴሞክራሲ በአገሪቱ የሚገኙ ሁሉንም አናሳም ሆኑ ገናና ቡድኖች እንደ ግለሰቦች ስብስቦች ስለሚቆጥራቸው የእያንዳንዱን ግለሰብ መብት ለማክበር ሲል የሁሉንም ቡድኖች መብት ማስከበሩ አይቀርም። አብዮታዊ ዴሞክራሲ ገናና ቡደኖች በ አናሳ ቡድኖች ላይ የበላይነት እንዲኖራቸው የሚያደርግ ነው። ሊበራል ዴሞክራሲ ግን አናሳ ቡድኖችም ጭምር እያንዳንዳቸው ሊክበሩ  የሚገባቸው ግለሰቦች ስብስቦች በመሆናቸው መብታቸው እንዲከበር ያደርጋል። ዋናው የሊበራል  ዴሞከራሲ ጥንካሬ አድርጌ የምቆጥረው የፈጠራ ክህሎትን የማሳደግ ባህሪው ነው። የግለሰቦችን ሃብት ንብረት የማፍራትና ያፈሩትም ሃብት በመንግስትም ሆነ በሌላ ካቅማቸው በላይ በሆነ አካል ከመነጠቅም ሆነ ተጽእኖ ከመደረግ ጥበቃ የሚያደርግ በመሆኑ ግለሰቦች በነፃነት የመመራመርና የመፍጠር ባህሪ እንዲኖራቸው የሚያደርግ ነው። ከዚያም በላይ የሊበራል ዴሞክራሲ ዋነኛ መገለጫ የሆነው ለ አዳዲስ አስተሳሰብና ማህበራዊ እሴቶች ክፍት መሆኑ ነው። ከ19ነኛው ክ/ዘመን ወዲህ ከተከሰቱ ዋነኛ ፈጠራዎችና ግኝቶች ከዘጠና በመቶ በላይ የሚሆኑት ሊበራል ዴሞክራሲን ባሰፈነችው በ አሜሪካ ነው የተከሰቱት። ይህ የሆነበት ዋነኛ ምክኒያት ያለው ስርአት ፈጠራን የሚያበረታታ በመሆኑ ነው። ሆኖም ሊበራል ዴሞክራሲም የራሱ ድክመት አለበት። በተለይ የ እያንዳንዱን ዜጋ እንዲሁም አናሳም ሆነ ገናና ቡድን መብት ማስጠበቅ ዋነኛ ባህሪው ሰለሆነ የእያንዳንዱን ባለድርሻ ስጋት ለማስታመም ሲባል በሊበራል ዴሞክራሲ የሚመጣ ለውጥ እጅግ ጎታታ ሊሆን ይችላል። በተለይ ለግለሰቦች ሃብት ጥበቃ ስለሚያደርግ እንደ አብዮታዊ ዴሞክራሲ መንግስት የ አገሪቱን ሃብት እንደፈለገው እንዳያዝበት ያግደዋል። ይህ ደግሞ የ አገሪቱን ሃብት በወሳኝና አስፈላጊ ሴክተሮች እያዋሉ ሊመጣ የሚችለውን ፈጣን እድገት ያጓትተዋል። በተለይ ከ እለት ጉርስ አልፎ የተሻለ ነገርን ለመፍጠር የሚጥር መካከለኛ ገቢ ያለው ህብረተሰብ ባልተፈጠረበት ሁኔታ የ አገሪቷን ሃብት ማስተባበር ካልተቻለ ባለንበት መርገጥ ወይም የሁዋሊዮሽ መጓዝ ሊመጣ ይችላል።

ባጠቃላይ መልኩ አሁን ባገራችን ሁለት ተፎካካሪ ርእዮተ አለሞች  እንዳማራጭ ቀርበዋል። “አብዮታዊ ዴሞክራሲ”ና “ሊበራል ዴሞክራሲ”። አብዮታዊ ዴሞክራሲን የሚያራምደው ኢህአዴግ አገሪቱን በመጪዎቹ ሁለት አሰርት አመታት መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ ትመደብ ዘንድ የ አገሪቱን ሃብት በተገቢው ቦታ እያዋልኩ እሰራለሁ እያለን ይገኛል። ባልከፋ ነበር። ነገር ግን የጠየቀን ዋጋ ከፍተኛ ነው። የ እያንዳንዳችንን መብት ነው የጠየቀን። በኢኮኖሚያዊ እድገትና በዴሞክራሲ መሃል እንድንመርጥ እያስገደደን ይገኛል። በሌላ በኩል የሊበራል ዴሞክራሲ አራማጅ የሆኑት እንደ ኢዴፓ ያሉ ፓርቲዎች ድንቅ የሆነ አማራጭ ፖለቲካዊ መስመር ቢያቀርቡም ያን መስመራቸውን የሚያስፈፅሙበት ጡንቻቸው እጅግ የቀጨጨ መሆን ለዴሞክራሲ ብለን ኢኮኖሚያዊ እድገቱን የማጣት ስጋት ደቅኖብናል።

ስለሆነም ለ አገሪቱ የሚበጀው በሁለቱም በኩል ወደቀናው አቅጣጫ መሻሻል ካለ ነው። በ ኢህአዴግ በኩል ዴሞክራሲን ከማስፈን አኳያ ከ1997 እስከ 2002 ዓ.ም. የተከተላቸውን ዴሞክራሲያዊ እድገቱን የሚያፍኑ እርምጃዎች መመርመር ይጠበቅበታል። በተለይ በገፍ አባላትን የመመልመልና እያንዳንዱ አባል አምስት አምስት ግለሰቦችን እንዲቆጣጠር የተነደፈው ስትራቴጂ ባስቸኳይ መቀየር ይኖረበታል። የፓርቲ አባላትን ቁጥርና ብቃት በተገቢው ሁኔታ ማስተካከልና መንግስታዊና ፓርቲያዊ መዋቅርን መለየት አገሪቱ በ አሃዳዊ ፓርቲ ወይስ በመድብለ ፓርቲ ስርአት ውሰጥ እንዳለች መለኪያ ስለሆነ ባስቸኳይ መፍትሄ ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ነው። በ አገሪቱ የግል ኤሌክትሮኒክ ሜዲያ እንዲስፋፋ ሁኔታዎችን ማመቻቸትም የግድ ነው። ገዢው ፓርቲ በነዚህና በሌሎችም መሰረታዊ ጉዳዮች ላይ የፖሊሲም የህግም የ አስተሳሰብም ለውጥ ካደረገ በሌሎች መስኮች ካስመዘገባቸው ስኬቶች ጋር ተዳምሮ ለወደፊቱ የሚያስመሰግነው ይሆናል። የሊበራል ዴሞክራሲ አራማጅ የሆኑ ፓርቲዎች ሊበራል ዴሞክራሲ ከ አገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ የሚጣጣምበትን ሁኔታ በማጥናት የጀመሩትን የ አይዲዮሎጂ ምርምር በስፋትና በጥልቀት መቀጠል ይኖርባቸዋል። ከሁሉም በላይ አላማቸውን ለማሳካት የሚያስችላቸው አደረጃጀትና ብቃት መፍጠር ላይ ከፍተኛ ስራ መስራት ይጠበቅባቸዋል። በተለይ የ ኢትዮዽያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) በአገሪቱ ሊበራል ዴሞክራሲን በማራመድ ረገድ ፋና ወጊ ከመሆኑ አንፃር የተሻለ ብቃት ስላለው ተመሳሳይ ርእዮተ አለም ያላቸውን የፖለቲካ ሃይሎች በማሰባሰብና አቅምን በማጎልበት ረገድ ብዙ መስራት ይጠበቅበታል።  

መርስኤ ኪዳን

mersea.kidan@gmail.com  

ሃምሌ 2002 ዓ.ም.

 

 

Comments