ሕገ -መንግስትና ሕግ የማይስማሙባት አገር ::

Home         Mission      Coffee House        Radio & TV        Entertainment        Contact         Photo Gallery

 አቶ በላይነህ ተካልኝ (ስሙ ተቀይሯል ) ተወልዶ ያደገበትን ደብረ ኤልያስ ቀበሌ ገበሬ ማኅበር (ምዕራብ ጐጃም ዞን ) ለቆ ሥራ ፍለጋ ወደ ደቡብ ክልል የተጓዘው የአሥራ ስድስት ዓመት ታዳጊ ወጣት በነበረበት 1987 . . ነው፡፡ የተሻለ ኑሮ ፍለጋ የትውልድ ቀየውን ጥሎ የሄደው ይኼው ወጣት ወደ ደቡብ ክልል አምርቶ ለስድስት ዓመታት ያህል በቡና ለቃሚነትና በከብት እረኝነት ተቀጥሮ በማገልገል ከእጅ ወደ አፍ የሆነ ሕይወት ሲመራ ቆይቷል፡፡ 1993 . . ግን አቶ በላይነህ ከተቀጣሪነት ወጥቶ የራሱን ሕይወት በራሱ የሚመራበት ዕድል ተፈጠረለት፡፡ እሱና በደቡብ ክልል የሚኖሩ ሌሎች እሱን መሰል የአማራ ክልል ተወላጆች የመሬት ባለቤት መሆን እንደሚችሉ የሚያበስረው ዜና ሲደርሳቸው ዜናውን አምነው መቀበል አልቻሉም ነበር፡፡

  1993 . . በፊት በደቡቡ ክልል ቤንቺ ማጂ ዞን ውስጥ ጉራፋርዳ ተብሎ የሚጠራ ቦታ አልነበረም፡፡ በአሁኑ ወቅት በጉራፋርዳ ወረዳ የሚተዳደሩት የሚኒጥ ብሔረሰቦች 1993 . . በፊት ይተዳደሩ የነበሩት በሸኮ ወረዳ ሥር ነበር፡፡ እነዚህ ብሔረሰቦች ‹‹በሸኮ ወረዳ ሥር አንተዳደርም ራሳችን በራሳችን ማስተዳደር አለብን፤›› የሚል ጥያቄ ሲያነሱ፣ ‹‹ራሳችሁን በራሳችሁ ለማስተዳደር መስፈርቱ የሚጠይቀውን የሕዝብ ብዛት አታሟሉም፤›› የሚል ምላሽ ይሰጣቸዋል፡፡ እንደዚህ ዓይነት ተስፋ አስቆራጭ መልስ የተሰጣቸው የብሔረሰቡ አባላት ግን ሞኞች አልነበሩምና ‹‹ራሳችንን ማስተዳደር አንችልም›› ብለው እጃቸውን አጣጥፈው አልተቀመጡም፡፡ ከዚያ ይልቅ ራሳቸውን ለማስተዳደር የሚያስችል የሕዝብ ብዛት ማግኘት የሚያስችላቸውን ዘዴ ማጠንጠን ጀመሩ፡፡ ብዙም ሳይቸገሩ መልሱን አገኙ፡፡ ከሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል መጥተው ደቡብ ክልል ውስጥ በሚገኙ የተለያዩ ወረዳዎች በቡና ለቀማና በተለያዩ የጉልበት ሥራዎች የተሰማሩ በርካታ የአማራ ክልል ተወላጆች መኖራቸውን የሚያውቁት የሚንጥ ብሔረሰብ አባላት፣ ‹‹ወደ እኛ ወረዳ መጥቶ በልማት ሥራ ላይ መሰማራት የሚፈለግ ኢትዮጵያዊ ዜጋ በሙሉ ይምጣና አካባቢውን ያልማ፤›› የሚል ማስታወቂያ ይለጥፋሉ፡፡ ይህንን ዜና የሰሙ የአማራ ክልል ተወላጆችም ነገ ዛሬ ሳይሉ ወደ ሸኮ ወረዳ አመሩ፡፡ ህልማቸው የሰመረላቸው የቀበሌና የወረዳ አመራሮችም ለልማት የሚውል መሬት በሕጋዊ መንገድ እየሸነሸኑ አከፋፈሉ፡፡ ከሰሜን ክልል የመጡ በርካታ ሰዎችን በአካባቢያቸው ማስፈር የቻሉት የሚኒጥ ብሔረሰቦችም ምኞታቸው ተሳክቶ ራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደር መብት አገኙ፡፡ ወረዳቸውም ጉራፋርዳ ተባለ፡፡

 

በላይነህ ተካልኝ እንደሚለው፣ የጉራፋርዳ ወረዳና የቀበሌ አመራሮች ለእሱና ለሌሎች ሰፋሪዎች የሰጧቸው መሬት በማንም ይዞታ ስር ያልነበረ የበረሃ ሳር የሚበቅልበት ቦታ ነበር፡፡ በአካባቢውም ምንም ዓይነት መሠረተ ልማት አልነበረም፡፡ የራሳቸው መሬት ባለቤት ሆነው በግብርና ሥራ ተሰማርተው ሕይወታቸውን የመቀየር ህልምና ጉጉት የነበራቸው እነዚህ ዜጐች ግን ችግሩን ተቋቁመው በተሰጣቸው መሬት ላይ ቡና፣ ፓፓያ፣ አቮካዶ፣ ሙዝና የመሳሰሉትን ተክሎች በመትከልና የተለያዩ ሰብሎችን በማምረት የሰንበሌጥ ሳር ብቻ ይበቅልበት የነበረውን አካባቢ ወደ ገነትነት ቀየሩት፡፡ አትክልትና ፍራፍሬ በአካባቢው በሽ ሆነ፡፡ በጥረታቸው የራሳቸውን ብቻ ሳይሆን የአካባቢውንም የኑሮ ዘይቤ ቀየሩ፡፡

በወቅቱ 4.5 ሔክታር መሬት የተረከበው አቶ በላይነህም ሁለት ሔክታሩን ለቡና ተክል ቀሪውን 2.5 ሔክታር መሬት ደግሞ ለእርሻ በመጠቀም በቆሎ፣ በርበሬ፣ ሩዝና የመሳሰሉትን ምርቶች በማምረት ሕይወቱን ለወጠ፡፡ ሀብትና ንብረት ማፍራት ሲጀምርም ትዳር መሥርቶ ልጆችን ወለደ፡፡ ጉልበቱን ተጠቅሞ ባፈራው ንብረት ጥቂት የደስታ ዓመታት ያሳለፈው አቶ በላይነህና ሌሎች እሱን መሰል ከሰሜን የአገሪቱ ክፍል የመጡ ሰፋሪዎች ግን የጀመሩትን የደስታ ሕይወት አጣጥመው መቀጠል አልቻሉም፡፡

 ክልል መስተዳድር ባስተላለፈው መመርያ መሠረት 1999 . . በኋላ በጉራፋርዳ የሰፈሩ የአማራ ክልል ተወላጆች በቀበሌና በወረዳ ኃላፊዎች በሕጋዊ መንገድ ያገኙትን መሬት እንዲለቁና አካባቢውን ጥለው እንዲሄዱ፣ 1999 . . በፊት መጥተው በጉራፋርዳ ወረዳ ስር በሚገኙ የተለያዩ ቀበሌዎች የሚኖሩ ሰፋሪዎች ደግሞ ሁለት ሔክታር መሬት ብቻ ይዘው እንዲቀጥሉ ተደርጓል፡፡ ይህንን ውሳኔ ተከትሎ ጥረው ግረው አካባቢውን ያቀኑ በብዙ ሺሕ የሚገመቱ በርካታ የሰሜን አካባቢ ተወላጆች በኃይልና በጉልበት አካባቢውን ለቀው እንዲወጡ ተደርጓል፡፡ አሁንም እንዲወጡ እየተደረገ ነው፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን የፌዴራል መንግሥትም ሆነ የአማራ ክልል ባለሥልጣናት አንድም ነገር ትንፍሽ አላሉም፡፡ ለፌዴራል መንግሥት አቤቱታ ለማቅረብ ባለፈው ሐሙስ ወደ አዲስ አበባ የመጡ ተፈናቃዮችም ከድጡ ወደ ማጡ እንዲሉ በአራት አውቶቡስና በአንድ ሚኒባስ ታጭቀው ባለፈው ሳምንት ዓርብ ወደ ደብረ ብርሃን ተጓጉዘዋል፡፡ እነዚህ ዜጐች አሁን በምን ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ የሚታወቅ ነገር የለም፡፡

 

ዜጐች ከቦታ ቦታ ተዘዋውረው የመኖርና ሀብት የማፍራት መብት እንዳላቸው ሕገ መንግሥቱ ቢደነግግም፣ በደቡብ ክልል መስተዳድር የወጣው አዲስ አዋጅ ይህንን መብት በሚጥስ መልኩ እየተተገበረ መሆኑን የተለያዩ የፖለቲካ ተንታኞች ይናገራሉ፡፡ መሳይ በቀለ የተባሉ የፖለቲካ ተንታኝ ይህንን ጉዳይ አስመልክተው በድረ ገጽ ላይ ባወጡት ጽሑፍ፣ ‹‹በራስህ አገር ውስጥ እንዴት ስደተኛ ትሆናለህ ?›› ሲሉ ከጠየቁ በኋላ እንደ ኢትዮጵያ ዓይነት ከዲሞክራሲ ሥርዓት ጋር መተዋወቅ በጀመሩ አገሮች የማይከሰት ነገር እንደሌለ ይገልጻሉ፡፡ ዜጐች የሌላ ብሔር አባላት ስለሆኑ ብቻ ይኖሩበት ከነበረው ቀዬ እንዲለቁ ማድረግ ከባድ የሰብዓዊ መብት ጥሰት መሆኑን በጽሑፋቸው ያመለከቱት አቶ በቀለ፣ ከብሔር ጋር በተያያዘ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ለሚካሄደው የሰብዓዊ መብት ጥሰት ገዢው ፓርቲ ተጠያቂ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡

ገዢው ፓርቲ ኢሕአዴግ ብሔርን መሠረት ባደረገ መልኩ የተለያዩ ክልሎች እንዲፈጠር ማድረጉ ዜጐች ለአንድ ዓላማ ከመሥራት ይልቅ እርስ በእርስ በጥላቻ እንዲተያዩ ያደረገ መሆኑን የሚናገሩት እኚሁ ጽሐፊ፣ ‹‹ስለቤንቺ ማጂ ስትሰሙ ምንድን ነው የምታስቡት ? ብስጭት ? ድብታ ? መደናገር ? ተስፋ መቁረጥ ? በአሁኑ ወቅት ሥልጣን የያዙት የኢትዮጵያ መሪዎች የሚፈልጉትን ማድረግ እንደሚችሉ ታያላችሁ፡፡ እነዚህ መሪዎች ከዚህ አድራጐታቸው እንዲቆጠቡ ማድረጊያው ብቸኛው መንገድ ድርጊታቸው ጉዳት እንደሚያስከትል ማሳየት ነው፡፡ ለመጥፎ ድርጊት የሚከፈል ዋጋ አለ፤›› በማለት በደቡቡ ክልል መስተዳደር የተፈጸመው ክስተት አደጋ ሊኖረው እንደሚችል ያስገነዝባሉ፡፡

 ኑሮአቸውን በዩናይትድ ስቴትስ የመሠረቱት አቶ መሳይ ከኢትዮጵያ በተለየ መልኩ የህብር መፍጠር (Melting Pot) ጽንሰ ሐሳብ የምትከተለው አሜሪካ የተለያዩ ማኅበረሰቦች ህብር ፈጥረው አንድ የጋራ ባህል ያላቸው ሕዝቦች የሚኖሩባት አገር መሆኗ ለታላቅነቷ መሠረት እንደሆነ ቀጣዩን ምሳሌ በመጥቀስ ያስረዳሉ፡፡ ‹‹በሳምንቱ መጨረሻ የሜዲካል ጉዳይ ስለነበረኝ ወደ ሆስፒታል ሄጄ ነበር፡፡ እኔ ታማሚው ከኢትዮጵያ የመጣሁ ነኝ፡፡ እኔን የተቀበለችኝ ነርስም ኢትዮጵያዊት ነች፡፡ የመረመረችኝ ሴት ናይጄሪያዊት ነች፡፡ ኤክስሬይ ያነሳኝ ሰው ደገሞ ከኤርትራ የመጣ ነው፡፡ የድንገተኛ ሐኪሜ ደግሞ ነጭ አሜሪካዊ ነው፡፡ ከሆስፒታሉ የምወጣበትን ሒደት ያመቻቸችው ሴት ደግሞ ሂስፓኒክ (ከመካከለኛውና ከላቲን አሜሪካ ተወላጅ ) ነች፡፡ ሆስፒታሉ የሚሠራው እንደ እንከን አልባ ማሽን ነው፤›› በማለት አሜሪካ የተለያዩ አገር ዜጐችን ‹‹እንኳን ደህና መጣችሁ›› ብላ በመቀበል ለብልፅግናና ለሃያልነት መብቃቷን የሚያስረዱት አቶ ይልማ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ግን በተቃራኒው የቤንች ማጂ ዞን አስተዳዳሪዎች የራሳቸውን ዜጐች ሀብትና ንብረት በመቀማት ‹‹ወደ መጣችሁበት ተመለሱ›› የሚል ትዕዛዝ ማስተላለፋቸው አገሪቱ ወደ መጥፎ መንገድ እያመራች መሆኑን እንደሚያመላክት ይገልጻሉ፡፡

የኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ ሙሼ ሰሙ በበኩላቸው፣ ዜጐች ከቦታ ቦታ ተዘዋውረው የመኖርና ሀብት የማፍራት መብታቸው በሕገ መንግሥቱ በተደነገገበት ሁኔታ ይቅርና ይህንን መብት የማያጐናጽፍ ሕግ ባይኖር እንኳን በተለያዩ ክልሎች የሚኖሩ ዜጐች እንደዜጋ ህልውናቸውን ሊጠብቅ እንደሚገባ ይናገራሉ፡፡

‹‹ማንኛውንም ዜጋ ሠርቶ ለመኖር የሚያስችል መብትን የሚያሳጣ ድርጊት በሕግም መልክ ቢሰፍር ስህተት ነው፤ ሊሻሻል ይገባል፤›› የሚሉት አቶ ሙሼ፣ አንድን አገር የሚያስተዳድር መንግሥት ይህንን የዜጎችን መሠረታዊ ፍላጐት የማያስከብር ከሆነ ድርጊቱ የሰብዓዊ መብት ጥሰት መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ እርሳቸው እንደሚሉት፣ ዜጐች ከአገራቸው ወጥተው በተለያዩ አገሮች በመኖር በነፃነት ሥራ ሠርተው ሕይወታቸውን የሚቀይሩበት ዕድል በተፈጠረበት በአሁኑ ወቅት፣ በራሳቸው አገር ውስጥ ጉልበታቸውን አፍስሰውና ዕድሜያቸውን ጨርሰው ያቀኑትን መሬት ለቃችሁ ሂዱ ማለት ከባድ ስህተት ነው፡፡

‹‹ዜጐቹ ዕድሜያቸውን፣ ጉልበታቸውንና ሀብታቸውን በማፍሰስ የመሬቱን ዋጋ (Value) ጨምረዋል፤›› የሚሉት አቶ ሙሼ፣ ከዓመታት በኋላ ያለሙትን መሬት ትተው እንደገና ሕይወትን ‹‹›› ብለው እንዲጀምሩ መደረጉ በየትኛውም መንገድ ተቀባይነት ሊኖረው እንደማይችል ይገልጻሉ፡፡ የዜጐቹ በአካባቢው መኖር በአገር ደኅንነት ችግር የሚያስከትል ወይም ደግሞ ግጭት የሚፈጥር ሆኖ ቢገኝ እንኳን ሰፋሪዎቹ ተገቢው ካሳ ተከፍሏቸው እንዲሁም ተለዋጭ ቦታ ተሰጥቷቸው በተገቢው መንገድ አካባቢውን እንዲለቁ መደረግ እንዳለበት አቶ ሙሼ አክለው ያስረዳሉ፡፡

‹‹የአካባቢ ተወላጅ ያልሆኑ ዜጐችን የማፈናቀሉ ዕርምጃ ከየአካባቢው የሚመነጭ ከሆነ የኢትዮጵያዊነት ትርጉሙ ምንድነው ?›› ሲሉ የሚጠይቁት አቶ ሙሼ፣ በመሬት ባለቤትነት ከመኖር መብት ጋር በተያያዘ በክልሎች ከሚወጡ ሕጐች ይልቅ ሕገ መንግሥቱ ቅድሚያ ሊሰጠው እንደሚገባ ይናገራሉ፡፡ በጉራፋርዳ ወረዳ የተወሰደው ዜጐችን የማፈናቀል ዕርምጃ በየትኛውም ክልል የሚኖሩ ዜጐችን የመኖር ሥነ ልቦና የሚያዳክም መሆኑን ሲያስረዱም፣ ‹‹ሁኔታው በዚህ መልኩ ከቀጠለ ነገ አዲስ አበባ የእኔ ነው የሚል አካል ተነስቶ የአካባቢው ተወላጅ ያልሆኑ ዜጐች ይውጡ ቢል ምን ሊከሰት ይችላል፤›› ሲሉ የጉዳዩን አሳሳቢነት ይገልጻሉ፡፡ አያይዘውም ጉዳዩ ከዚህም አልፎ ሉዓላዊነትን በማስከበር ረገድ ከፍተኛ ችግር ሊፈጥር እንደሚችል ይናገራሉ፡፡

‹‹አንድ ዜጋ እንደ ዜጋ ዳር ድንበርን የማስከበር ጥያቄ ሲቀርብለት ጥሪውን ተቀብሎ የሕይወት መስዋዕት የሚከፍለው በማንኛውም ክልል ላይ የመኖርና ሀብት የማፍራት መብት አለኝ ብሎ ስለሚያምን ነው፡፡ አለበለዚያ ጉዳዩ የተወረረው ክልል ጉዳይ ብቻ ይሆናል፡፡ ወደ ፊት የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት በማስከበር ረገድ የራሱን ችግር ይፈጥራል፤›› ሲሉ ሊከሰት የሚችለውን አደጋ ይገልጻሉ፡፡ በጉራፋርዳ ይኖሩ የነበሩ አብዛኛዎቹ ሰፋሪዎች በቀበሌና በወረዳ አመራሮች በሕጋዊ መንገድ መሬት ተሰጥቷቸው በግብርና ሥራ ላይ ተሰማርተው የቆዩ ናቸው፡፡ የክልሉ ኃላፊዎች ራሳቸው በፈቀዱላቸው ቦታዎች ላይ የሰፈሩትን እነዚህን ዜጐች ሕገወጥ ናችሁ የሚሉበት ምክንያት ጉዳዩን ለሚከታተሉት ዜጐች አሁንም እንቆቅልሽ ነው፡፡ የክልሉ ፕሬዚዳንት አቶ ሽፈራው ሽጉጤ ራሳቸው 1999 . . በኋላ በቤንች ማጂ ዞን ኑሮአቸውን የመሠረቱ ሰፋሪዎች መሬቱን በቀበሌም ይሁን በወረዳ ኃፊዎች ፈቃድ ያገኙ ቢሆንም፣ ከአካባቢው መልቀቅ እንዳለባቸው ትዕዛዝ አስተላልፈዋል፡፡ እዚህ ላይ ነው እንግዲህ ‹‹ሕገወጡ ማነው ?›› የሚል ጥያቄ የሚያስነሳው፡፡
ምንጭ ( ሪፖርተር ) ::
Comments