ኣርቲስት ሃመልማል ኣባተ በቢሮክራሲው በመማረሯ ኣዲስ ዜማ ልትለቅ ነው ።

Home         Mission      Coffee House        Radio & TV        Entertainment        Contact         Photo Gallery

ቀበሌ ስሄድ የሚመለከተው ክፍለ ከተማውን ነው ይሉኛል፤ ክፍለ ከተማ ስሄድ ደግሞ እኛን አይመለከተንም፤ የሚመለከተው አስተዳደሩን ነው ይሉኛል፤ አስተዳደሩ ዘንድ ስሄድ ደግሞ ይኼማ የክፍለ ከተማው ሥራ ነው ይሉኛል፤›› ያለችው አርቲስት ሐመልማል አባተ፣ ለመንግሥትና ለኢትዮጵያ ሕዝብ ፍትሕ ማጣቷን ለማሳወቅ አንድ ነጠላ ዜማ በቅርቡ እንደምትለቅ ለሪፖርተር አስታወቀች፡፡ አርቲስቷ ‹‹ፍትሕ አጣሁ›› የምትልበት ጉዳይ የተጀመረው ከሦስት ዓመታት በፊት መሆኑን ገልጻለች፡፡ ከሦስት ዓመታት በፊት በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ቀበሌ 20/21 (በድሮው) ውስጥ 640 ካሬ ሜትር ቦታ ከግለሰብ ትገዛለች፡፡ ‹‹ቦታውን ስገዛ ከፊት ለፊቴም፣ ከገዛሁት ቤት ጀርባም በማስተር ፕላኑ የተረጋገጠ መንገድ ነበረው፤›› ትላለች፡፡በማታውቀውና የከተማውን ማስተር ፕላን ባልጠበቀ ሁኔታ ለአንድ ግለሰብ ከፊት ለፊቷ ያለው ቦታ ተሰጥቶ ሕንፃ መገንባቱን የገለጸችው አርቲስት ሐመልማል፤ የአካባቢው ነዋሪዎች ፍሳሽ የሚወገድበት ቱቦ በመዘጋቱ ያለፉትን ሁለትና ሦስት ክረምቶች ጐርፍ በቤታቸው ውስጥ እየገባ ማሳለፋቸውን ተናግራለች፡፡

‹‹
ውኃ ወደ ላይ አይፈስም›› የምትለው አርቲስቷ፣ ‹‹ለውጥ ነው›› በሚል የተሠራው የፍሳሽ ማስወገጃ የሚያስገርምና ሕግና ሥርዓት ባለበት አገር የማይፈጸም ሥራ መሆኑን ጠቁማለች፡  ችግሩ በጣም ስለበዛባቸው የሠፈሩ ሽማግሌዎች በመሰብሰብ ቀበሌ፣ ክፍለ ከተማ፣ ማዘጋጃ ቤትና ኢሕአዴግ /ቤት ድረስ ቢሄዱም፣ አንዱ በአንዱ ላይ ከማሳበብ የዘለለ ውሳኔ አለማግኘታቸውን ሐመልማል ገልጻለች፡፡  የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አቶ ኩማ ደመቅሳ ዘንድ ሄዳ፣ ‹‹እንዴት ማስተር ፕላኑን የጣሰ ሥራ ይሠራል?›› በሚል ባስቸኳይ እንዲስተካከል ትዕዛዝ አስተላልፈውላት እንደነበር የገለጸችው አርቲስቷ፤ ‹‹እስካሁን ግን ምንም መፍትሔ አላገኘሁም፤›› ብላለች፡፡ ቀበሌው ከክፍለ ከተማው፣ ክፍለ ከተማው ከቀበሌው ጋር ምንም ግንኙነት እንደሌላቸውና ከላይ የሚወርድን ትዕዛዝ የሚያስፈጽም አካል አለመኖሩን የገለጸችው አርቲስቷ፤ በሁሉም ተቋሞች ውስጥ ያሉ ሀቀኛ ሠራተኞች የእኔን ግራ መጋባት በማየት ‹‹በሽምግልና ተስማሙ›› እንዳሏት ተናግራለች፡፡

‹‹
የመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣን (አቶ ኩማንና የኢሕአዴግ /ቤትን) ወስኖ የላከው ደብዳቤ ላይ ሽምግልና ምን አመጣው?›› የምትለው ሐመልማል፤ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ማስተር ፕላኑን ካልጠበቀ ‹‹ቤተ መንግሥትም ቢሆን ይናዳል›› ባሉት መሠረት በእነሱም ሠፈር ማስተር ፕላኑን ዘግቶ የተገነባው ሕንፃ መፍረስ እንዳለበት ያላትን እምነት ተናግራለች፡፡የተጻፈ ሕግ ባለበት አገር አስፈጻሚ ጠፍቶ ዜጐች ከወዲያ ወዲህ መንገላታታቸው በጣም አሳዛኝ መሆኑንና እሷም እንዳዘነች የገለጸችው ሐመልማል፤ በሦስቱም ተቋማት ላለፉት ሦስት ዓመታት ስትመላለስ ያያት ሁሉ ‹‹አሁንም አልጨረሽም?›› የሚል ጥያቄ እንደሚያቀርብላት ገልጻለች፡፡ተቆጭተውና ተጸጽተው ሊረዱ የሚሞክሩ አንዳንድ ሀቀኛ ሠራተኞች በሦስቱም ተቋማት ውስጥ መኖራቸውን የገለጸችው ሐመልማል፤ ብቻቸውን ግን ምንም ማድረግ እንደማይችሉ መገንዘቧን ተናግራለች፡፡

ቦታው ለመኖሪያና ለቢዝነስም አገልግሎት ይሆናል በሚል ከሦስት ዓመታት በፊት የገዛችው ቦታ ያለምንም አገልግሎት መቀመጡ የሚያደርሰው ጉዳት በሷ ላይ ብቻ ሳይሆን በመንግሥትም ጭምር መሆኑን የገለጸችው ሐመልማል፤ ‹‹ዓይን አውጥተው ጉቦ የጠየቁኝ ሰዎች ቢኖሩም እኔ ያለኝ ኃይል ሙዚቃ ነውና ነጠላ ዜማ እለቃለሁ እንጂ ብር አልሰጥም፤›› ብላለች፡፡‹‹የላይኛው ትዕዛዝ በታችኛው አካል የማይፈጸም ከሆነ ምን ይደረጋል?›› ካለች በኋላ በነጠላ ዜማ ልትለቅ ያሰበችውን ግጥም ማዘጋጀቷን ገልጻልናለች፡፡
‹‹
የዛፉ ሸንጐ የጥላው ሥር፣
ጥንቱን ቢያስቡት ይሻል ነበር፡፡
ዛሬ ቀበሌ ክፍለ ከተማ፣
ተብሎ ሲነገር ፍትሕ ፈጻሚ ሰው የለማ፡፡
አቤት አገሬ አቤት እማማ፣
ለሸንጐ እሚሆን በይ ስሪ አውድማ፡፡
ፍቅር መሆኑ ሳያነጋግር፣
ኢትዮጵያዊነት ባለም ሲነገር፣
ሰሚ መጥፋቱ ታዲያ ምንድነው
መዘጋጃ ቤት፣ ክፍለ ከተማ ብሎም ቀበሌ ሥራው ምንድነው?›› የሚለው ከነጠላ ዜማው የተወሰደ ስንኝ ነው፡፡

አርቲስት ሐመልማል የድሮ ሽማግሌዎች የሚገባውንና መባል ያለበትን በማለት እንደሚያስማሙ ገልጻ፤ ሕግ የማያዋጣ እየሆነ ከሄደ ምርጫው ‹‹ሁለት ነው›› ብላለች፡፡ ሕገወጥ መሆን ወይም አገር ጥሎ መሄድ፡ , የበላይ አካላት የጻፉትን ትዕዛዝ የሥር ኃላፊ ‹‹እነሱ የጀመሩትን እንዴት እኔን ፈጽም ይሉኛል?›› በማለት ቁጭ እንደሚያደርገው የገለጸችው አርቲስቷ፣ ኅብረተሰቡን ይጠቅማሉ ተብለው የተቋቋሙት ተቋማት ለመጉዳት ከዋሉ ምንም አገልግሎት እንደሌላቸው መታወቅ እንዳለበትና መፍረስ እንዳለባቸው ተናግራለች፡፡ ‹‹ይኼን ያህል ብር ስጭኝ ያለኝ ባለሥልጣን አለ፤ አሁን ስሙን ባልጠቅስም በቅርቡ ግን ይፋ አደርገዋለሁ፤›› ብላለች፡፡

ቦታውን ሄደው ማየታቸውን፣ በፊት ለፊቷ የተገነባውንም ሕንፃ መመልከታቸውንና በክረምት ወቅት የሚመጣው ፍሳሽ በጣም አስቸጋሪ መሆኑን መመልከታቸውን የገለጹልን የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ አወቀ ኃይለ ማርያም ናቸው፡፡በአርቲስት ሐመልማል ይዞታ ፊት ለፊት ሕንፃ የገነባው ግለሰብ ለፓርኪንግ በሚል አጥሮ ይዞት የነበረውን ቦታ ካርታውን እንዲመክን ማድረጋቸውን የተናጋሩት አቶ አወቀ፤ እሷ በፊት ለፊቷ ያለውን የፓርኪንግ ቦታ መጠቀም እንደምትችልም እንደአማራጭ አቅርበዋል፡፡በቅርቡ ተገነባ በተባለው ሕንፃ ፊትም ሆነ በስተጀርባ ያሉ ቤቶችና ባዶ ቦታዎች ጸድተው ማስተር ፕላኑ እንደገና እንደሚታይ የገለጹት አቶ አወቀ፤ ማስተር ፕላኑን የሚነካ ሆኖ ከተገኘ ሕንፃው እንደሚፈርስ አስታውቀዋል፡፡

የማስተር ፕላኑ ሁኔታ ሳይረጋገጥ ግለሰቡ የገነባውን ሕንፃ ማፍረስ ተገቢ እንደማይሆን የሚገልጹት ምክትል ሥራ አስኪያጁ፤ ግለሰቡ ሕንፃውን ሊገነባ የቻለው የቀድሞ ሊዝ ቦርድ ወስኖ ቦታውን እንደሰጠውና ‹‹ሕጋዊ ነኝ›› እንደሚል ጠቁመዋል፡፡

ችግሩን መቶ በመቶ የፈጠረው ክፍለ ከተማው መሆኑን ያረጋገጡት አቶ አወቀ፣ መጀመሪያውኑ ማስተካከል ይገባው እንደነበር ተናግረዋል፡፡ በቅርቡ አካባቢው እንደሚጸዳና ሐመልማልም ብትሆን ደረጃውን የጠበቀ ሕንፃ መገንባት እንደሚገባት አሳስበዋል፡፡የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ጀማል ሳላህን በስልክ አግኝተን ስለተፈጠረው ችግር ለማነጋገር ብንሞክርም፣ ‹‹እኔን አይመለከተኝም፤ በቀጥታ የሚመለከተው የይዞታ አስተዳደር የሥራ ሒደት መሪ አቶ ክብረአብ አሰፋን ነው›› በማለታቸው አቶ ክብረአብን አግኝተን አነጋግረናቸዋል፡፡ እሳቸውም ‹‹እኔ ከኃላፊነቴ ወደ ሌላ ቦታ ተዛውሬ አቶ ታምራት ተስፋዬ የሚባሉ ሰው የመሬት አስተዳደር /ቤት ኃላፊ ሆነው ስለተሾሙ በሚቀጥሉት ሳምንታት አነጋግሯቸው፤›› በማለታቸው የክፍለ ከተማው ምላሽ ሊገኝ አልቻለም፡፡   ምንጭ ( ሪፖርተር)

Comments