ጠ/ሚ/ር መለስ ዜናዊ የስኴር ኮርፕሬሽንና ኢንጂነሪንግ ኮርፕሬሽን በኔ ትእዛዝ ስር ይሁን አሉ::

Home         Mission      Coffee House        Radio & TV        Entertainment        Contact         Photo Gallery

የኢትዮጵያ ስኳር ልማት ኤጀንሲ በድጋሚ በኮርፖሬሽን መዋቅር ተደራጅቶ ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ሊሆን ነው፡፡ ኤጀንሲው ኮርፖሬሽን ሆኖ እንዲደራጅ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ያዘዙ ሲሆን፣ የአዲሱን ኮርፖሬሽን አወቃቀር 30 የሚጠጉ የሚጠኑ ባለሙያዎች በማጥናት ላይ መሆናቸውን የሪፖርተር ምንጮች ገልጸዋል፡፡

ኤጀንሲው በኮርፖሬሽን ደረጃ ሲደራጅ አራቱን ዓመታት ጊዜ ውስጥ በአገሪቱ ሊገነቡ የታቀዱትን የሦስት አዳዲስ ስኳር ፋብሪካዎች ግንባታ ኮርፖሬሽኑ በበላይነት  እንደሚያካሂድ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡


አዳዲሶቹ ስኳር ፋብሪካዎች 200 ሺሕ ሔክታር መሬት ላይ የሚካሄዱ የሸንኮራ አገዳ ልማት የሚኖራቸው ሲሆን፣ ቦታዎቹ የሚገኙት በአማራ ክልል ጣና በለስ ተፋሰስ አካባቢ፣ በኦሮሚያ ክልል በደዴሳ ሸለቆ አካባቢና በደቡብ ክልል ደቡብ ኦሞ አካባቢ ነው፡፡


በአሁኑ ወቅት እንደገና በኮርፖሬሽን የሚዋቀረው የስኳር ዘርፍ በወታደራዊው መንግሥት ወቅት የኮርፖሬሽን መዋቅር ነበረው፡፡ ኢሕአዴግ አገሪቱን ሲቆጣጠር ሦስቱ የስኳር ፋብሪካዎችም በፕራይቬታይዜሽንና በመንግሥት የልማት ድርጅቶች ተቆጣጣሪ ኤጀንሲ ሥር ሆነው እንዲተዳደሩ ሲደረግ፣ የስኳር ልማት ኮርፖሬሽኑ ደግሞ የኢትዮጵያ ስኳር ልማት ማስፋፊያ ድጋፍ ማዕከል ተብሎ ሲሠራ ቆይቷል፡፡


ማዕከሉ ከሦስቱ ስኳር ፋብሪካዎች ስኳር እየተረከበ ለገበያ የሚያቀርብ ሲሆን፣ በአብዛኛው ሲያካሂድ የቆየው ይህንኑ ሥራ ነበር፡፡


ከሁለት ዓመት በፊት በድጋሚ የኢትዮጵያ የስኳር ልማት ኤጀንሲ ተብሎ ሲደራጅ፣ የስኳር ፋብሪካዎቹ ተጠሪነታቸው ለሱ ሆነው የቀድሞውን ስኳር የመረከብና የመሸጥ ሥራ ሲያካሂድ ቆይቷል፡፡

በአዲሱ የኮርፖሬሽኑ መዋቅር መሠረት የፋብሪካዎቹን ሙሉ ኃላፊነትና ሥልጣን ይረከባል፣ የስኳር ልማትና የኢታኖል ምርት እንዲስፋፋ በማድረግ ለአገር ውስጥና ለውጭ ገበያዎች የማቅረብ ሥራ ያካሂዳል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ኤጀንሲው ቀደም ሲል ተጠሪነቱ ለንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የነበረ ሲሆን፣ በአዲሱ የመንግሥት መዋቅር የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የንግድ ሚኒስቴርና የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ተብሎ ለሁለት ተከፍሏል፡፡


ኤጀንሲው ንግድም የኢንዱስትሪ ልማትም የሚያካሂድ በመሆኑ፣ ከዚህ በኋላ ተጠሪነቱ ከሁለቱ ለአንዱ መሆን አይችልም፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በአዲሱ የኮርፖሬሽን መዋቅር መሠረት በርካታ ሥራዎች ስለሚኖሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቅርብ ሆነው ሥራውን መከታተል ይፈልጋሉ በማለት የኤጄንሲው አንድ የሥራ ኃላፊ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡


የስኳር ልማት ኤጀንሲ ዋናው ቢሮ ካለበት ከሜክሲኮ አደባባይ ወደ ልደታ በሚወስደው መንገድ ፊሊፕስ ሕንፃ አጠገብ ግዙፍ ሕንፃ የመገንባት ዕቅድ ይዟል፡፡ ‹‹ሹገር ሐውስ›› በሚል ስያሜ የሚጠራው ሕንፃ ግንባታ ፕሮጀክት 4500 ካሬ ሜትር ቦታ የሚፈልግ ሲሆን የቦታ ጥያቄው ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቀርቧል፡፡


ይሁንና በእስካሁኑ ሒደት የቦታው ጥያቄ ውሳኔ አላገኘም፡፡ ኤጀንሲው ለእዚህ ሕንፃ ግንባታ 330 ሚሊዮን ብር ወጭ ለማድረግ አቅዷል፡፡ ዲዛይኑን ኮሊግ ኮንሰልታንት ኩባንያ የሠራለት ሲሆን፣ ሕንፃው የቀጣዩ ኮርፖሬሽን ዋና ቢሮ ሆኖ ከማገልገሉ በተጨማሪ ሲኒማ ቤት፣ ሬስቶራንት፣ መደብሮችና የመሳሳሉ አገልግሎቶችን የሚሰጡ ክፍሎች ይኖሩታል፡፡


ከስኳር ኤጀንሲ በተጨማሪ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን ተጠሪነቱ እንዲሁ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ይሆናል፡፡ ኮርፖሬሽኑ እስካሁን ተጠሪነቱ ለማዕድንና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሆኖ ቆይቷል፡፡ በአዲሱ መዋቅር የሚኒስቴሩ የኢነርጂ ዘርፍ ከውኃ ሀብት ሚኒስቴር ጋር ተዋህዶ የውኃና የኢነርጂ ሚኒስቴር ተብሏል፡፡


ኮርፖሬሽኑ በዚህ መዋቅርም ቢሆን ተጠሪነቱ ለሚኒስቴሩ መሆን ቢችልም አሁን ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ነው እንዲሆን የተወሰነው፡፡


ሪፖርተር ያነጋገራቸው ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ባለሥልጣን እንደገለጹት፣ የስኳርና የኢነርጂ ዘርፎች በቀጣዩ አምስት ዓመታት ግዙፍ ግንባታ የሚካሄድባቸው በመሆናቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቅርበት ጉዳዩን መከታተል በመፈለጋቸው ነው በማለት ያስረዳሉ፡፡


በእርግጥ ስኳርን በሚመለከት ሦስቱ ስኳር ፋብሪካዎች የሚያካሂዱት የማስፋፊያ ፐሮጀክቶች አዲስ ከሚገነባው የተንዳሆ ስኳር ጋር ተዳምሮ የፋብሪካ ግንባታና አሁን ካለው 314.5 ሺሕ ቶን ስኳር 2007 ከሰባት እጥፍ በላይ በማሳደግ ወደ 2.2 ሚሊዮን ቶን የማድረስ ዕቅድ አለ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ሦስት አዳዲስ የስኳር ፋብሪካዎች ይገነባሉ፡፡ ኢነርጅን በሚመለከትም አሁን ካለው ሁለት ሺሕ ሜጋ ዋት ከአምስት ዓመት በኋላ እስከ ስምንት ሺሕ ሜጋ ዋት የሚደርስ ኃይል ለማመንጨት የሚያስችሉ ግንባታዎች ለማካሄድ ታቅዷል፡፡
 

በሁለቱ ተቋማት የሚካሄደው ግንባታ ግን በዋናነት የሚቀናጀው አዲስ በተቋቋመው የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን አማካኝነት ነው፡፡


ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ለኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽኑ ብርጋዴል ጀነራል ክንፈ ዳኘውን ሹመዋል፡፡


በብርጋዴር ጄነራሉ የሚመራው አዲሱ ኮርፖሬሽንም ተጠሪነቱም ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ነው፡፡ በዚህ ኮርፖሬሽን አማካኝት ለሚካሄዱ የፋብሪካ ግንባታም ሆኑ ለኃይል ማመንጫ ግንባታዎች የሚያስፈልጉ ምርቶች ኮርፖሬሽኑ አገር ውስጥ እንዲመረት ያደርጋል፡፡


አገር ውስጥ ሊመረት የማይችለው ብቻ ነው አገር ውስጥ እንዲገባ የሚፈቀደው፡፡  በተለይ የሦስቱን ኮርፖሬሽኖች ሥራ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቅርብ ለመከታተልና ውሳኔ ለመስጠት በሚል በእሳቸው ሥር እንዲሆን እንደተደረጉ የመንግሥት ባለሥልጣናት ያምናሉ፡፡


የመጪዎቹ አምስት ዓመታት ስትራቴጂካዊ ዕቅድ እንደሚገልጸው፣ ከአምስት ዓመታት በኋላ የአገሪቱን ኢኮኖሚን የመምራቱን ተግባር ከግብርና የሚረከበው ኢንዱስትሪ ነው፡፡ ኢንዱስትሪው ደግሞ መሠረቱን ለመጣል ያሰበው በተለይ የኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን በሚያካሂደው ሥራ ላይ ነው፡፡ ምንጭ (ሪፖርተር)
 
Comments