በገና ጾም ፍቺ ዩነቨርስቲ ውስጥ ረብሻ ተነስቶ ነበር::

Home         Mission      Coffee House        Radio & TV        Entertainment        Contact         Photo Gallery

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሳይንስ ፋኩልቲ ተማሪዎች በገና በዓል አከባበር ምክንያት ከዩኒቨርሲቲው ኃላፊዎች ጋር ባለመስማማታቸው፣ ታህሣሥ 27 ቀን 2003 ዓ.ም. ከቀኑ 11 ሰዓት አካባቢ ጀምረውት የነበረውን ረብሻ የአዲስ አበባ ፖሊሶችና ፌዴራል ፖሊስ በመተባበር በቀላሉ ተቆጣጠሩት፡፡ በተለይ የኦርቶዶክስ እምነት ተከታይ የሆኑት ተማሪዎች በየዓመቱ ይደረግላቸው የነበረው የፆም መፍቻ ዝግጅት በዚህ ዓመት እንደማይደረግላቸው ታህሣሥ 25 ቀን 2003 ዓ.ም. ሲገለጽላቸው፣ በማግስቱ ታህሳስ 26 እና 27 ቀን 2003 ዓ.ም. የምግብ አድማ ሲያደርጉ ቆይተው ታኅሣሥ 27 ቀን ምግብ ለመመገብ ወደ ካምፓሱ ካፌ የገቡትን ተማሪዎች በመቃወም ረብሻ ማንሳታቸውን አንዳንድ ተማሪዎች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡  ወደ ተማሪዎች መመገቢያ አዳራሽ (ካፌ) የገቡትን ተማሪዎች በመቃወም ተማሪዎቹ ድንጋይ በመወርወራቸው የአዳራሹ መስታወቶችና የቤተ መጻሕፍት ሕንፃ መስታወቶች መሰባበራቸውን ተማሪዎቹ አረጋግጠዋል፡፡  በጥናት ላይ እንደነበረች በተወረወረ ድንጋይ የቤተ መጻሕፍቱ ሕንፃ መስታወት ሲሰበር ማየቷንና በድንጋጤ በሥላሴ ቤተክርስቲያን በኩል ባለው በር ወጥታ መሄዷን የገለጸችልን አንዲት ተማሪ፣ ‹‹ሁሉንም ነገር በንግግርና በመግባባት መፍታት ሲቻል፣ ተማሪዎቹ በዩኒቨርሲቲው ንብረት ላይ ያደረሱት ጥፋት አግባብ አይደለም፤›› ስትል ድርጊቱን አውግዛለች፡፡

ከሰዓት በኋላ 11 ሰዓት አካባቢ ተማሪዎቹ ፈጥረውት በነበረው ግርግር የፖሊስ ኃይል ፈጥኖ በመድረስ ለአንድ ሰዓት ያህል ከቅድስት ማርያም እስከ ትምህርት ሚኒስቴር ድረስ ያለውን መንገድ በመዝጋት፤ በዩኒቨርሲቲው ውስጥ የነበረውን ግርግርና ረብሻ ከተቆጣጠረ በኋላ፣ በዩኒቨርሲቲው በኩል ያለውን መውጪያና መውረጃ መንገድ በመዝጋት በአንድ በኩል (በዩኒቨርሲቲው በፊት ለፊት) ያለውን መንገድ ለእግረኛ መንገዱንም ለተሽከርካሪ ክፍት አድርጓል፡፡  ታህሣሥ 28 ቀን 2003 ዓ.ም (በማግስቱ) በፋኩልቲው አካባቢ ተገኝተን የነበረውን ችግርና አጠቃላይ ሁኔታ ለማጣራት እንደሞከርነው፤ ፖሊስ፣ የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላትና የዩኒቨርሲቲው ኃላፊዎች ችግሩን በቀላሉ ለመፍታት (ስምምነታቸውን አላወቅንም) በመቻላቸው ተማሪዎች ነገ ለሚጀመረው የግማሽ ሴሚስተር ፈተና ለመዘጋጀት ሲወጡና ሲገቡ ተመልክተናል፡፡

ተፈጠረ የተባለውን ችግር ወደ ረብሻ ከመለወጥ ለምን በመነጋገርና በመመካከር ማስተካከል እንዳልቻሉ ተማሪዎቹን ጠይቀናቸው፤ በታህሳስ ወር መጀመርያ አካባቢ ለወትሮው ይደረግ የነበረው የገና በዓል ዝግጅት በዚህ ዓመት እንደማይደረግ ሲነገራቸው፣ ፒቲሽን ተፈራርመው ታህሳስ 8 ቀን 2003 ዓ.ም. ለተማሪዎች ዲን አስገብተው እንደነበር ተናግረዋል፡፡ ታህሳስ 8 ቀን 2003 ዓ.ም. ላስገቡት ጥያቄ ታህሳስ 25 ቀን 2003 ዓ.ም. ዝግጅቱ እንደማይደረግ በመግለጽ ምላሽ እንደተሰጣቸው የገለጹት ተማሪዎቹ፤ ለዘመናት ሲደረግ የነበረ ዝግጅት ለእነሱ መከልከሉ ስላናደዳቸው ወደማይፈለግ እንቅስቃሴ ውስጥ ሊገቡ መቻላቸውን ተናግረዋል፡፡  በ2000 ዓ.ም. ተመሳሳይ ችግር ገጥሞ በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ አዳራሽ የገና በዓልን ማክበራቸውን የገለጹት ተማሪዎቹ፣ ፓርትያርኩ ለዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ለፕሮፌሰር አንድሪያስ እሸቴ በጻፉላቸው ደብዳቤ መሠረት ተስተካክሎ፣ በ2001 እና በ2002 ዓ.ም. በፋኩልቲው ቅጥር ግቢ ውስጥ ማክበራቸውን አስታውሰዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው በተለይ ለሚፆሙ ተማሪዎች እርድና የሙዚቃ ባንድ በማዘጋጀት በየዓመቱ በዓሉን ያከብር እንደነበርም ተናግረዋል፡፡

በዩኒቨርሲቲውና በተማሪዎቹ መካከል አለመስማማት የተፈጠረበትን ምክንያት እንዲገልጹልን የፋኩልቲው ተጠባባቂ ዲን የሆኑትን ፕሮፌሰር ገዛኸኝ ይርጉን አግኝተን ለማነጋገር ያደረግነው ጥረት ‹‹ከተማሪዎቹ ጋር ናቸው›› በማለት የኮሙኒኬሽን ኃላፊዎችን እንድናነጋግር ፀሐፊያቸው ነገሩን፡፡ የአካዳሚክ ፕሬዚዳንቷ አገር ውስጥ ስለሌሉ ተወካዩን የአካዳሚክ ምክትል ፕሬዚዳንት ዶ/ር ተካልኝ ወልደማርያምን ለማግኘት ጥረት ብናደርግም ‹‹ስብሰባ ላይ ናቸው፤ ወጣ ብለዋል፣ ስልክ እያነጋገሩ ነው›› ከሚል የፀሐፊ ምላሸ በስተቀር ልናገኛቸው አልቻልንም፡፡  ምንጭ ( ሪፖርተር)
Comments