አዋጅ! በትምህርት ጥራት ላይ!!

Home         Mission      Coffee House        Radio & TV        Entertainment        Contact         Photo Gallery

በቅርቡ የማኅበራዊ ጥናት መድረክ  “የከፍተኛ ትምህርት ጥራት በኢትዮጵያ የሕዝብ ተቋማትበሚል ርዕስ መጽሐፍ አሳትሞ ነበር፡፡ መጽሐፉ የትምህርት ጥራትን የተመለከቱ ጥናታዊ ጽሑፎችን የያዘ ሲሆን፣ ቀልቤን የሳበው እና ያስደነገጠኝ የአዲስ ተማሪዎችን ብቃት በተመለከተ የተካተተው መረጃ ነው፡፡ ዝርዝር ትንተናውን ለኋላ አቆይቼ በሁለት ሰንጠረዦች ላይ ያየሁትን ብቻ ላካፍላችሁ፡፡ መረጃው የተገኘው ከአገር አቀፍ ፈተናዎች ድርጅት መሆኑን ጽሑፉ ያመለክታል፡፡

ሠንጠረዥ 2 የአጠቃላይ 2 ደረጃ ብሔራዊ ፈተና የተማሪዎች ውጤት በጥሬ ማርክ/ከመቶ/

ዓመት

25 በታች ያገኙ

26-50ያገኙ

50 በላይ ያገኙ

75 በላይ ያገኙ

1999

44%

48.9%

7.6%

0.01%

2000

58%

36.6%

3%

0.07%

ይህን ቁጥር ስታዩ መቼም ራሳችሁን ሳትይዙ አትቀሩም፡፡ 1999 .. ብሔራዊ ፈተናውን ከወሰዱት ተማሪዎች መካከል 92.4 በመቶው ፈተናውን ወድቀዋል! 2000 ደግሞ 97 በመቶው ፈተናውን አላለፉም፡፡ ይባስ ብሎም 2000 .. ወደ 60 በመቶ የሚጠጉት ተማሪዎች 25 ከመቶ እንኳን ማግኘት አልቻሉም!! ይህን ውጤት ሳይ መጀመሪያ የመጣብኝ ስሜት፣  መንግሥት ለምን ትምህርት ቤቶቹን  ዘግቶ ችግሩን በጥልቀት አይመረምርም የሚል ነበር፡፡ እንደ እኔ እንደ እኔ ጉዳዩ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሁሉ ሳያስፈልገው አይቀርም ነበር፡፡ ይህን አይነት ውጤት ያላቸውን ተማሪዎች ይዞ የት መድረስ ይቻላል??

ነገር ግን ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚደለደሉትን ተማሪዎች ሁኔታ ስመለከት ደግሞ የመንግሥት ርምጃ ተቃራኒውን ሆኖ ነበር ያገኘሁት፡፡ የሚከተለውን ሰንጠረዥ ተመልከቱ

ሠንጠረዥ 3 የከፍተኛ ትምህርት መግቢያ ፈተና የተማሪዎች ውጤት ትንተና /500 ጥሬ ማርክ/

ዓመት

250 በታች ያገኙ

251-300ያገኙ

300 በላይያገኙ

መግቢያ ፈተና ከወሰዱት ውስጥ የተደለደሉ

1998

57.5%

32.5%

10%

97%

1999

46.3%

38.4%

15.3%

63.8%

2000

69.6%

22.2%

8.2%

88.1%

እግዜር ያሳያችሁ! 2000 .. የመግቢያ ፈተናውን ያለፉት ተማሪዎች 22.2 በመቶ ቢሆኑም ዩኒቨርሲቲ የገቡት ግን 88.1 በመቶ ናቸው፡፡  በሌላ አነጋገር 65.9 በመቶ የሚሆኑት ወዳቂ ተማሪዎች አለአግባብ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተደልድለዋል፡፡ ስለሆነም በዚህ ዓመት ከገቡት ተማሪዎች መካከል ሁለት ሶስተኛው ዩኒቨርሲቲ መግባት የማይገባቸው ነበሩ ማለት ነው፡፡ ከቀሪው አንድ ሦስትኛ መካከልም አብዛኛው ፈተናውን እንደነገሩ ያለፈ /50 እስከ 60 በማግኘት/ ተማሪ ነው፡፡ በመግቢያ ፈተናው 60 በመቶ በላይ ያመጡትእንቁተማሪዎቻችን /ድንቄም እንቁ!/  8.2 ከመቶ ብቻ ከሆኑ  ተማሪ ቤቶቻችንን ለምን ወደ ሌላ ትርፋማ የስራ ዘርፍ አይዛወሩም? /በሰማንያዎቹ አጋማሽ የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ የነበሩ ሰው የተግባረ ዕድ ትምህርት ቤት መምህራንን ሲያስፈራሩ፣እኛኮ ለናንተ ብለን ነው እንጂ ብንፈልግ ትምህርት ቤቱን ዘግተን ህንጻውን ማከራየት እንችላለንብለው እንደነበር የሰማሁትን አስታወሰኝ/፡፡

ብዙ መምህራን ጓደኞቼ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎቻቸውን የፈተና ወረቀት ሲያርሙ እዬዬያቸውን የሚያወርዱበት ምክንያት የገባኝ አሁን ነው፡፡ የመመረቂያ ወረቀት ስራ ቢዝነስም ለምን እንደተሰፋፋ የተገለጠልኝ አሁን ሳይሆን አይቀርም፡፡ መቼም ብዙዎቻችን የትምህርት ጥራት መውረዱን እንገነዘባለን፣ እናማርራለንም፡፡ ግን እንዲህ ራስ እስኪያዞር መውረዱን የምናውቅ አልመሰለኝም፡፡

መንግሥት ቀጣዩ የከፍተኛ ትምህርት የትኩረት አቅጣጫ 70 በመቶው በተፈጥሮ ሳይንስ እና ምህንድስና ዘርፍ፣ 30 በመቶው ደግሞ በማኅበራዊ ሳይንስ ዘርፍ እንደሆነ ነግሮናል፡፡ ተማሪዎቹስ ለእነዚህ ዘርፎች ብቁ ይሆኑ ይሆን? እስኪ የወደፊቱን ለመገመት ያህል ያለፈውን ውጤት እንይ፡፡

ሠንጠረዥ 2.2 የአጠቃላይ 2 ደረጃ ብሔራዊ ፈተና የተማሪዎች አማካይ ውጤት በትምህርት አይነት /በፐርሰንት/

ዓመት

ቋንቋ

ሒሳብ

ሳይንስ

ማኅበራዊ ሳይንስ

አማካይ ውሁድ ውጤት

1999

33.6%

18.91%

26.97%

32.2%

29.3%

2000

29.4%

17.97%

22.7%

22.6%

24.95

ጉዳችንን እዩት እንግዲህ፡፡ ውጤቱ ከአመት አመት እያሽቆለቆለ ሄዶ፣ ኢንጅነሮቻችንና ዶክተሮቻችን እንዲሆኑ የምናሰለጥናቸው ተማሪዎች፣ በርካቶቹ በሂሳብ 19 ከመቶ ማግኘት ያቃታቸው፣ በሳይንስ 25 ከመቶ እንኩዋን የሌላቸው ናቸው፡፡ የማኅበራዊ ሳይንስ ባለሙያዎቻችን እንዲሆኑ የሚታሰቡትም እንዲሁ 25 ከመቶ ማግኘት ያቃታቸው ተማሪዎች ሆኑ፡፡ በዚህ አይነት ምን አይነት መሐንዲስ፣ ምን አይነት ዶክተር፣ ምን አይነት ኢኮኖሚስት ይኖረን ይሆን? ጉዳቱን የበለጠ የሚያደርገው ደግሞ የሚቀጥለውን ትውልድ የሚያንጹት እነዚሁ ልጆቻችን መሆናቸው ነው፡፡

የችግሩን መጠን ለማሳየት ቀንጨብ አድርጌ አቀረብኩት እንጂ ጽሑፉ ሌሎችንም ተመሳሳይ አስደንጋጭ አሀዞች ይዟል፡፡ ርዕሱን ሳስብ ትዝ ያለኝ የፕሮፌሰር መስፍንየክህደት ቁልቁለትየሚለው መጽሐፍ ነበር፡፡ ይህንንስ ምን እንበለው ይሆን? የትምህርት ቁልቁለት?

ለመሆኑ ችግሩ የት ነው? ስርዓተ ትምህርቱ ለተማሪዎች የማይመጥን ሆኖ ነው? ምናልባት ፈተናው አለቅጥ ከብዶ ይሆን? አስተማሪዎቻችን ብቃት ያልነካቸው ስለሆኑ ይሆን? የፕላዝማ ቲቪ ጦስ እንደሆነስ? የተማሪ እና መምህር ምጣኔ ችግርስ ሊሆን አይችልም? አሁንስ መንግስት ምን ርምጃዎች ወስዷል? ተቃዋሚ ፓርቲዎቻችን ይህን ጉዳይ ያውቁታል? ሲያነሱትስ ተሰምተዋል? ዝርዝሩን እናንተና ባለሙያዎቹ ተመራመሩበት፡፡ ምንጭ ( አዲስ ነገር)
Comments