ህዝቡ መንግስት ላይ ሰላማዊና ህጋዊ ግፊት ማድረግ አለበት:: ( ኢደፓ)

Home         Mission      Coffee House        Radio & TV        Entertainment        Contact         Photo Gallery

በኢትዮጵያ የተከሰተውን የኑሮ ውድነት ዘላቂ መፍትሔ ያገኝ ዘንድ ሕዝቡ በመንግሥት ላይ ሰላማዊና ሕጋዊ ግፊት እንዲያደርግ የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) ጥሪ አቀረበ፡፡ በሰሜን አፍሪካ አገሮች የሚታየው ዓይነት የፖለቲካ ቀውስ በአገራችን እንዳይከሰት መንግሥት ከኑሮ ውድነት ጋር ተዛማጅ የመፍትሔ ዕርምጃዎችን በስፋትና በፍጥነት እንዲወስድ ኢዴፓ አሳስቧል፡፡
የኢዴፓ ሊቀመንበር አቶ ልደቱ አያሌው ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ሕዝቡ ከአመፅ ጋር ያልተያያዘ ግፊት በመንግሥት ላይ ማድረግ አለበት፡፡ ኢኮኖሚያዊ ችግር ወደ ፖለቲካዊ ችግር ሊቀየር ስለሚችል ይህ ለመንግሥት ስጋት ነው ብለዋል፡፡ አክለውም ሕዝቡ እስካሁን ድረስ ያደረገው ግፊትም ይህን ዓይነት ለውጥ ማምጣት ከቻለ በዚሁ መቀጠል እንዳለበት ገልጸዋል፡፡ መንግሥትም በሰሜን አፍሪካ አገሮች የተፈጠረው ሁኔታ እዚህ እንዳይደገም ተገቢ ምላሽ ሊሰጥ ይገባል ሲሉ ተናግረዋል፡፡  መንግሥት ለጡረተኞችና ለመንግሥት ሠራተኞች ባለፈው ረቡዕ ያደረገው የደመወዝ ጭማሪ በአገሪቱ ከተከሰተው ከፍተኛ የኑሮ ውድነት ጋር የማይመጣጠንና ዘግይቶ የመጣ እንደሆነ ኢዴፓ አስታውቋል፡፡ ሆኖም መንግሥት የወሰደው ዕርምጃ የኑሮ ውድነትን ከማቃለል አኳያ እንደበጐ ዕርምጃ ሊታይ ይገባል ሲል ፓርቲው ገልጿል፡፡+

የሲቪል ሰርቪስ ሚኒስትሩ አቶ ጁነዲን ሳዶ የመንግሥት ሠራተኛው የኑሮ ውድነቱን መቋቋም እንዲችል ከጥር 1 ቀን 2003 .. ጀምሮ ተግባራዊ የሚሆን የደመወዝ ማሻሻያ መደረጉን መግለጻቸው ይታወሳል፡፡ ሚኒስትሩ እንዳስታወቁት፣ ጭማሪው በዓመቱ መጀመሪያ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይህንኑ አስመልክቶ የተናገሩትን ተፈጻሚ የሚያደርግ ነው፡፡ ኢዴፓ ላለፉት አራት ዓመታት ለመንግሥት ሠራተኞችና ለጡረተኞች የደመወዝ ጭማሪ እንዲደረግ መንግሥትን በተደጋጋሚ መጠየቁን ገልጾ፣ 2002 የምርጫ ዘመቻ ወቅት ፓርቲው የደመወዝ ጭማሪውን ጉዳይ በማንፌስቶው ማካተቱን አስታውቋል፡፡ መንግሥትም በወቅቱ የኢዴፓን ጥያቄ ቢያጣጥለውም፣ አሁን ዕርምጃ መውሰዱ ተገቢ ነው ብሏል፡፡

ሆኖም መንግሥት በአሁኑ ወቅት እየወሰዳቸው የሚገኙ ዕርምጃዎች ከተዛማጅነት፣ ከፍጥነትም ሆነ ከመጠን አኳያ የኑሮ ውድነትና የዋጋ ግሽበት ችግሮችን ለመፍታት በቂ እንዳልሆኑ ገልጿል፡፡  የመንግሥት ሠራተኞችና የጡረተኞች መነሻ ደመወዝ 500 ብር ያነሰ መሆኑ ተገቢ አይደለም ብሎ ኢዴፓ እንደሚያምንም ገልጿል፡፡ ፓርቲውም የራሱን ጥናት አካሂዶ በምርጫ ማኒፌስቷቸው ላይ በግልጽ እንዳሰፈረው፣ በአሁኑ ወቅት አንድ ራሱን ችሎ የሚኖር ሰው 1200 ብር ባነሰ ገቢ ወጪውን ሊሸፍን አይችልም ሲል ኢዴፓ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡ መንግሥት ይፋ ባደረገው የደመወዝ ጭማሪ መሠረት አነስተኛው የሲቪል ሰርቪስ ደመወዝ 420 ብር ሲሆን፣ ጣሪያው 730 ብር እንዲሆን ተወስኗል፡፡ ሆኖም ኢዴፓ የአንድ ሠራተኛ የወር ደመወዝ ቢያንስ 500 ብር ሊሆን ይገባዋል ብሏል፡፡ በተጨማሪም በተለያዩ የግል ሥራዎች ላይ የተሠማሩና በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ዜጐችም ተገቢ የደመወዝ ጭማሪ የሚያገኙበትን አሠራር መንግሥት ባስቸኳይ ተግባራዊ ማድረግ ይጠበቅበታል ሲል ኢዴፓ አሳስቧል፡፡

በአገሪቱ የተከሰተውን የኑሮ ውድነት በተሻለ ሁኔታ ለማቃለል መንግሥት ከነዳጅ ዋጋ ድጐማ፣ ከተጨማሪ እሴት ታክስ ክፍያና ከአቅርቦት ዕድገት ጋር የተያያዙ ሌሎች ዕርምጃዎችን ጨምሮ መውሰድ ይጠበቅበታል ሲል ኢዴፓ ገልጿል፡፡  መንግሥት አሁን ያደረገው የደመወዝ ጭማሪ በአገሪቱ የሚገኙ ከአንድ ሚሊዮን በላይ የመንግሥት ሠራተኞችን፣ ተሿሚዎችንና የሕዝብ ተመራጮችን ይመለከታል፡፡

መንግሥት የሕዝቡን የኑሮ ውድነት ለማቃለል በራሱ የልማት ድርጅቶች አማካኝነት በሚያመርታቸው ስኳርን፣ ሲሚንቶንና ብረትን በመሳሰሉ ምርቶች ላይ ትርጉም ያለው ቅናሽ ማድረግ እንዳለበት ኢዴፓ አሳስቧል፡፡    ምንጭ ( ሪፖርተር )
Comments